ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማትና በታዳሽ ኃይል ለዓለም የስኬት አርዓያ ሆናለች -የሮማኒያ አምባሳደር

አዲስ አበባ፤ የካቲት 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማትና በታዳሽ ኃይል ለዓለም የስኬት አርዓያ ሆናለች ሲሉ በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በሀይል በማስተሳሰር ረገድም ጉልህ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት ባለፉት ዓመታት በተገበረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ችላለች።

ይህ ተግባርም የዓለም የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል የተስተካከለ ምህዳርን ለመፍጠር ጉልህ ሚና አለው። ኢትዮጵያ በዚህ ተግባሯም ዓለም አቀፍ እውቅናዎችን አግኝታለች።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ወደ ልማት ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ስኬቶች ሀገሪቷን በዓለም ላይ እውቅና እያስገኘላት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም ድንቅ የአካባቢ ጥበቃ ስራ መሆኑን ጠቁመዋል፤የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር መረጃዎችን እያስፋፋን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የአረንጓዴ አሻራ ስኬቶች ሀገሪቷን በአረንጓዴ ልማት፣ በታዳሽ ሀይል ስራዎች ለሌሎች ሀገራት አርዓያ አድርጓታል ብለዋል።

አምባሳደሯ አክለውም ኢትዮጵያ በልማት ጎዳና ላይ መሆኗን ጠቁመው፤ በአዲስ አበባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተመዘገቡ ያሉ የልማት ውጤቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ የልማት እንቅስቃሳም በሌሎች የክልል ከተሞች እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን ጨምሮ በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች አዲስ አበባን እውነተኛ የአፍሪካ መዲናነቷን በተግባር ያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው በአፍሪካ ልዩ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ግድቡ ቀጣናውን በሀይል በማስተሳሰር ረገድም ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም