ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የሉዓላዊነት አደራ የማይነጠል ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ 

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ የባህር በር ማግኘት የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የታሪክና የሉዓላዊነት አደራ የማይነጠል ነው ሲሉ  የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት 130ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ባለበት መድረክ ላይ ነው።

የዓድዋ ድል ለሠራዊታችን የሁልጊዜም የድል ስንቅ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።

የዓድዋ ድሉ ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ህዝብ የነፃነት ጎህ የፈነጠቀና ሰብዓዊ ክብርን ያጎናጸፈ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያውያንን ጀግንነት በዓለም አደባባይ ያስመሰከረና የሀገር ፍቅር ጽናትን ለዓለም የገለጠ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑንም አውስተዋል። 

የዓድዋ አስተምህሮት ኢትዮጵያዊነትን የሚያነግስ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ዓድዋ አጉራ ዘለል ፖለቲካን፣ ሌብነትን፣ ውስልትናንና ሀኬትን እንደሚጠየፍ አስረድተዋል።

የዘንድሮውን በዓል  ስናከብር  የድሉ እሳቤ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ያለውን ከፍ ያለ ፋይዳ በማመላከት ጭምር መሆኑን አብራርተዋል።

አባቶቻችን የጥቁር ህዝቦችን ክብርና ነጻነት በመስዋዕትነት ማስከበራቸውን አስታውሰው፤ የዛሬው የዓድዋ ድል ትርጉም ነጻነትን በብልፅግና ማስዋብ፣ ለትውልዱ የሚተርፍ አኩሪ ተግባር መፈጸምና ማስተላለፍ  መሆኑንም ገልጸዋል።

ዓድዋን ስናስብ አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሉዓላዊነት የከፈሉትን ዋጋ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ የነበራቸውን ሰፊ ርዕይ ጭምር መሆን አለበት ብለዋል።

በዓድዋ ድል ማግስት የዲፕሎማሲ ትግል አንዱ ማጠንጠኛ የነበረው ኢትዮጵያ ከዓለም የምትገናኝበትን የባህር በር ባለቤትነትን የማረጋገጥ ጉዳይ መሆኑንም አውስተዋል።


 

ኢትዮጵያውያን የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ባደረጉት ተጋድሎ ሲታይ ታሪክ ለኢትዮጵያ መልካምና በጎ እንደነበር ነው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ።

ይሁን እንጂ በአልፎ ሂያጅ የፖለቲካ ስሌትና ኢትዮጵያዊነትን ባልዋጀ ሀሳብ ታሪካዊና ስትራቴጂካዊ መልህቃችንን እንዲሁም ጥቅሞቻችንን መስዋዕት አድርገን ቆይተናል ነው ያሉት።

የዓድዋ ድል ያስተማረን እንደ ባህር በር ባሉ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ከታሪክ ትክክለኛ ጎን መቆም መቻልን ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ትላንት በዓድዋ አውድማ ላይ የተገኘው ወታደራዊ ድል ዛሬ በኢኮኖሚያዊና በጂኦ-ፖለቲካዊ ድል ሊደገም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዘላቂና አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብት የዓድዋ ሰማዕታት ካወረሱን የታሪክ አደራ የማይነጠል ነው ሲሉም ጠቅሰዋል።

የሀገራችን የኢኮኖሚ ጥማት የሚረካውና የህዝቦቿ እጣ ፈንታ ብሩህ የሚሆነው ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ ወይም በየብስ እግረ-ሙቅ ያለመታሰሯን ስናረጋግጥ ብቻ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

እንደ ዓድዋ ጀግኖች ሁሉ ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የኢትዮጵያን ጥቅም ማብሰር ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ መንገዳችንና መሻታችን ሰላማዊና በአብሮነት ማደግ ነው ብለዋል።

የባህር በር ጥያቄያችንን የታሪክና የፍትሕ ጥያቄ አድርጎ መረዳት እንዲሁም የትውልድ ህልውና ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ወሳኝ ነው በማለት ተናግረዋል። 

ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ዓድዋ ምን ጊዜም የግጭት ግለት ለሚሹና ሰላምን በመዝገበ ልቦናቸው ላልከተቱ ሁሉ ታላቅ መካነ እውቀት መሆኑን አስረድተዋል።


 

የዘመናችን ጀግንነትም የጭቅጭቅ ጩኸትን የሚያሰማ ሳይሆን፤ የሀገር ፍቅርን፣ እውቀትንና አብሮነትን የሚያጎላ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ለሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማብሰር የዘመኑ የዓድዋ ድል መሆኑን ጠቁመው፤ ጉዳዩ የትውልድ ህልውና መሆኑን መረዳት ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊነትን ከእውቀትና ከአብሮነት ጋር አዋህዶ መጓዝ የትውልዱ አደራ መሆኑን በመግለጽ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም