የዓድዋ ድል ለሠራዊታችን የሁልጊዜም የድል ስንቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል ለሠራዊታችን የሁልጊዜም የድል ስንቅ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል ለሠራዊታችን የሁልጊዜም የድል ስንቅ ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ገለጹ።
ድሉ የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ብስራትና የሰው ልጅ የክብር ማህተም መሆኑንም ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሐውልት ስር የአበባ ጉንጉን አኖሩ
የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፤ ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ድል ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት እና የሰው ልጅ ለክብሩ የከፈለው መስዋዕትነት በድል የተመሰከረበት የታሪክ ማማ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓድዋ ድል የተባበረ ህዝብ ዘመናዊና የታጠቀን ወራሪ ኃይል ድል በማድረግ፣ የማይሸነፍ ወራሪ የለም የሚል የሞራል የበላይነትን ለመላው ዓለም ያስመሰከረ ታላቅ ስኬት ነው ብለዋል።
አባቶቻችን በዓድዋ ተራሮች ላይ የከፈሉት መስዋዕትነት የአፍሪካን ክብር በማስመለስና አህጉራዊ አንድነትን በማጽናት ዛሬ ለደረስንበት አህጉራዊ የመከላከል አቅምና የጋራ ትብብር ዋነኛው የመንፈስ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ነው ያሉት።
የአፍሪካ መከላከያ ሚኒስትሮች በበዓሉ ላይ መገኘታቸውም ድሉ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንና የመላው ዓለም የጋራ የነጻነት የድል በዓል መሆኑን በተግባር የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
የዛሬው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአባቶቹን የጀግንነት አደራ ተሸክሞ የሚገኝ የታሪክና የጀግንነት ውጤት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት በፅኑ መሠረት ላይ ከማቆም ባለፈ በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የነጻነት ዘብ በመሆን የማይተካ መስዋዕትነት እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዓድዋ ለሠራዊታችን የታሪክ ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በመላው አባላቱ የጀግንነት ወኔ በዲሲፕሊኑ እና በአይበገሬነቱ ውስጥ ህያው ሆኖ የሚኖር የሁልጊዜም የድል ስንቅ ነው ብለዋል።
የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሀሳብ መከበሩ፣ የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ የወረሰውን የነፃነት ገድል ወደ ላቀ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት በስራ ወደ ሀገራዊ ከፍታ ሊያሸጋግረው እንደሚገባ የሚያመላክት መሆኑን ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል።
ትላንት በዓድዋ ተራሮች ላይ የተገኘው ድል ዛሬ ለምናስመዘግበው ስኬት ዋነኛ የስነ-ልቦና ስንቅ መሆኑንም ተናግረዋል።
የታሪክ አደራን በውጤት የታጀበ ኩራት አድርጎ ለሚቀጥለው ትውልድ ማውረስም የዚህ ዘመን የዓድዋ ቃል ኪዳን ነው ብለዋል።