ቀጥታ፡

አዲሱ ትውልድ በዓድዋ ድል ተከብራ የኖረችውን ኢትዮጵያ ወደ ላቀ ከፍታ ማሸጋገር አለበት - ልጅ ዳንኤል ጆቴ  

አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ አዲሱ ትውልድ በዓድዋ ድል ተከብራ የኖረችውን ኢትዮጵያ ወደ ላቀ ከፍታ ማሸጋገር አለበት ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ገለጹ።

130ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ፣ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ  ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።  

የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የብርታት እና የሞራል ምንጭ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ፤ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የዛሬ 130 ዓመት በጣሊያን ጦር የተቃጣውን ጥቃት በአሸናፊነት መንፈስ በድል መደምደማቸውን  አውስተዋል፡፡በእነርሱ የሕይወት መስዋዕትነት የሀገር ዳር ድንበር መከበሩንም ተናግረዋል።

በዓለም ላይ ስሙ የገዘፈው የዓድዋ ድል በህዝቦች የጸና የሀገር ፍቅር ስሜትና ተጋድሎ የተገኘ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ኢትዮጵያ ነጻነቷን አጽንታ የቆየች የጀግኖች ምድር መሆኗን አስመስክራለች ብለዋል።

አሁንም ሀገራችንን ለመድፈር የሚቃጡ የጠላት ኃይሎች የዓድዋን ታሪክ እንዲመለከቱ ያወሱት ልጅ ዳንኤል፤ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ህልውና ላይ እንደማይደራደሩ በመገንዘብ ትክክለኛ ካልሆነ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የአሁኑ ትውልድም በሀገር ሰላምና እድገት ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የኢትዮጵያን ብልፅግና ቀጣይነት ሊያረጋግጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ በወጣቶች እጅ ላይ ነው ያሉ ሲሆን ፥ አዲሱ ትውልድ የአያቶቹን አደራ ተቀብሎ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ የማሻገር ታላቅ ኃላፊነት እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም