የዓድዋን ድል ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልእኮ በላቀ ብቃትና ዝግጁነት ለመወጣት ዳግም ቃል በመግባት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋን ድል ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልእኮ በላቀ ብቃትና ዝግጁነት ለመወጣት ዳግም ቃል በመግባት ነው
አሶሳ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድልን ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልእኮ በላቀ ብቃትና ዝግጁነት ለመወጣት ዳግም ቃል በመግባት ነው ሲሉ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ተናገሩ።
የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የብርታት እና የሞራል ምንጭ ነው - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል "ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሃሳብ በአሶሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በመርሐግብሩ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላትና አመራሮች፣ የክልሉ አመራሮች፣ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች እና የተለያዩ የፀጥታ አካላት ተገኝተዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የታደሙት የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ጀግንነት የሚገለጥበት፣ የጠንካራ አንድነት ማሳያ እና በትውልድ ቅብብሎሽ የጀግንነት ስንቅ ሆኖ የሚዘከር መሆኑን ገልጸዋል።
በመከላከያ ሰራዊት ከ404ኛ ህዳሴ ኮር መቶ አለቀ ጋሻው አደነ፤ የዓድዋ ድል ጀግኖች አያቶቻችን ያለምንም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ ወራሪ ሀይሎችን በመመከት ለአሁኑ ትውልድ ትልቅ አሻራ ያኖሩበትና የመላ ጥቁር ህዝቦች የድል ብስራት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ከዚህ ታላቅ ድል የምንማረው አንድነትን በማጥበቅ፣ ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት በጋራ በመቆም የኢትዮጵያዊያን ህብረ ብሄራዊ አንድነት በተግባር የሚረጋገጥበት ስለመሆኑ አንስተዋል።
የዓድዋ ድልን ስናከብር የተሰጠንን ሀገራዊ ተልእኮ በላቀ ብቃትና ዝግጁነት ለመወጣት ዳግም ቃል በመግባት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ከኮሩ አባላት መካከል አስር አለቃ ለምለም ፋንታሁን፤ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ለሀገር ያላቸውን ፍቅር እና የሚከፍሉትን መስዋዕትነት ያስመሰከረ በመሆኑ ድሉ ሁልጊዜም የሚታወስ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአሁኑ ትውልድም የዓድዋ ድልን ከማክበር ባለፈ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሀገር እድገትና ማንሰራራት የላቀ ፋይዳ ያላቸውን ትላልቅ የልማት ስራዎች ለማሳካት በመዘጋጀት መሆን አለበት ብለዋል።
የ404ኛ ህዳሴ ኮር የመሃንዲስ መምሪያ ሻምበል መስፍን ጊታ፤ በዓድዋ ድል የተገኘውን ነፃነት እና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የመከላከያ ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ስለመሆኑ አረጋግጠዋል።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ምልክትና የመላ ጥቁር ህዝቦች የድል ብስራት መሆኑን ገልፀው፥ የአሁኑ ትውልድም በትብብርና በአንድነት በመቆም ምንም ነገር ማሳካት እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።