የዓድዋ ድል በባርነት ቀንበር ሥር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ነፃ እንዲወጡ መሰረት የሆነ ድል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል በባርነት ቀንበር ሥር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ነፃ እንዲወጡ መሰረት የሆነ ድል ነው
ጂንካ፤ የካቲት 23/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ በቅኝ ያለመገዛት ታሪክ ብቻ ሳይሆን በባርነት ቀንበር ሥር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ነፃ እንዲወጡ መሰረት የሆነ ድል መሆኑን የጂንካ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
የዓድዋ ድል ለሠራዊታችን የሁልጊዜም የድል ስንቅ ነው
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በመላው ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በጂንካ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም የዓድዋ ድል በዓል የሀገራችን ኢትዮጵያ የጀግንነት፣ የፅናት እና የአይበገሬነት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
አቶ ወንድማገኝ እሸቴ፥ የዓድዋ ድል በአል የትብብር፣ የፅናት፣የቆራጥነት እና የአይበገሬነት ማሳያ መሆኑን ነው የገለጹት።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ በቅኝ ያለመገዛት ታሪክ ብቻ ሳይሆን በመላው አለም ላይ በባርነት ቀንበር ሥር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ነፃ እንዲወጡ መሰረት የሆነ የጥቁር ህዝቦች ድል መሆኑንም አንስተዋል።
በክረ ትጉሃን መምህር ዮናስ አስመሮም በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል ወራሪ ጠላትን ድል ያደረግንበት የጦርነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ነጮች ለጥቁሮች ያላቸው የበታችነት አስተሳሰብ የተቀየረበትና አፍሪካውያን አቅም እንዳላቸው ጭምር ያሳየንበት ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድም እንደ ዓድዋ ሁሉ ጀግንነቱን በልማት እያሳየ መሆኑን ጠቁመው፥ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ የተሰሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች የዚህ ማሳያ እንደሆኑም አንስተዋል።
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀን ጠላት ያንበረከክነው ከዳር እስከ ዳር አንድ ስለሆንን ነው ያሉት ደግሞ ኮማንደር በኃይሉ ተካ ናቸው።
አንድነታችን ለድል አብቅቶናል ያሉት ኮማንደር በኃይሉ፥ ያሁኑ ትውልድም በሀገራዊ ጉዳይ ላይ አንድ በመሆን ለአንድ አላማ መሰለፍ እንዳለበት መክረዋል።
የታሪክ መምህሩ ፍጥረቱ ኃይሌ በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል ታሪክ በትውልዱ ውስጥ እንዲሰርፅ በመንግሥት እየተደረገ ያለው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የአለም ህዝብ ይህንን አኩሪ ታሪክ እንዲያስታውስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።