የዐድዋ ድል የአንድነት ማሳያ ታሪካዊ ምልክት ነው - የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የዐድዋ ድል የአንድነት ማሳያ ታሪካዊ ምልክት ነው - የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ የካቲት 23/2018 (ኢዜአ)፦ የዐድዋ ድል የአፍሪካ ሉዓላዊነት፣ ክብር እና አንድነት መገለጫ ታሪካዊ ምልክት ነው ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ አስገነዘቡ።
ዓድዋ በመልካምነት የተባበሩ ልቦች፣ በኅብረት የተሰለፉ ጀግኖች ድል ያስመዘገቡበት የጽኑ መንፈስና የከፍታችን ተምሳሌት ነው
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር 130ኛውን የዐድዋ ድል በዓል አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመልዕክታቸውም፤ የዐድዋ ድል የአፍሪካ ሉዓላዊነት፣ ክብር እና የአንድነት ታሪካዊ ምልክት ነው ብለዋል።
የዐድዋ ድል አፍሪካውያን በአይበገሬነት መንፈስ የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ ያሳዩበት መሆኑንም በአጽንኦት ገልጸዋል።
የዐድዋ ድል መንፈስ እና ታሪካዊ ዐሻራ በአጀንዳ 2063 ስር የአፍሪካ ህልሞች እንዲሳኩ የመሪነት ሚና አሁንም እየተወጣ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አፍሪካውያን ፈተናዎችን ለመሻገር በአንድነት መቆም እንዳለባቸው ገልጸው፤ አጋርነት የአኅጉሪቱ ትልቁ የጥንካሬ ዐቅም መሆኑን አስረድተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት በአህጉሪቱ ሰላም፣ ቀጣናዊ ትስስር እና የጋራ ብልፅግና እውን እንዲሆን አበክሮ እየሠራ መሆኑንም አመላክተዋል።