ቀጥታ፡

የዓድዋ ድል ገድል በትውልዱ ውጤታማ የልማት ሥራዎች ሊደገም ይገባል

 ጭሮ ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦የቀደምት አባቶች የዓድዋ ድል ገድል በትውልዱ ውጤታማ የልማት ሥራዎች ሊደገም እንደሚገባ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ወጣቶች ፅናትንና የአንድነትን ኃይል ከዓድዋ ጀግኖች ሊማሩ ይገባል

130ኛው የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ''ከአኩሪ  ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ'' በሚል መሪ ሀሳብ በሀገርአቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ ትምህርት ክፍል መምህር ኬንቦን ለሙ እንደገለጹት፣ የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ የማይበገሩ መሆናቸውን ያስመሰከረ ትውልዱ የሚኮራበት ታሪክ ነው።

ድሉ ለጥቁር ሕዝቦች ለፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል መንገድ የከፈተ በመሆኑ የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑንም አመልክተዋል።

የለውጡ መንግስት ይህን አኩሪ ታሪክ ለመዘከር የገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ትውልዱ ለልማት እንዲተጋና የራሱን ታሪክ እንዲሰራ መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል።

በዩኒቨርስቲው የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር መምህር መሐመድ ጀማል በበኩላቸው፣ የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ያጎናጸፈው የአይበገሬነት መንፈስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ሊደገም ይገባል ብለዋል።

የዳግማዊ ዓድዋ ምሳሌ የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የሕዝብ አንድነትና ጽናት ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ውጤታማ ለማድረግ የበለጠ መትጋት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን አመልክተዋል።

ትውልዱ የዓድዋን እሴቶች ወደ ተግባራዊ የልማት ስራዎች በመቀየር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ማረጋገጥ እንዳለበት ያነሱት ደግሞ በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪ ፈቃዱ ወርቁ ናቸዉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም