ወጣቶች ፅናትንና የአንድነትን ኃይል ከዓድዋ ጀግኖች ሊማሩ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ፅናትንና የአንድነትን ኃይል ከዓድዋ ጀግኖች ሊማሩ ይገባል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ ወጣቶች ፅናትንና የአንድነትን ኃይል ከዓድዋ ጀግኖች ሊማሩ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
130ኛው የዓድዋ ድል በዓልን በማስመልከት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከወጣቶች ጋር የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
የመከላከያ ትምህርት እና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ወጣቶች በመድረኩ ላይ ታድመዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ ወጣቶች የዓድዋን የጽናትና የአንድነት መንፈስ ለዛሬው የሀገር ግንባታ ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡
ዓድዋ የታሪክ ማስታወሻ ብቻ ሳይሆን ዛሬም ድረስ የምንመራበት የፅናት መንፈስ መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በባለቤትነት በመያዝ ዓድዋ በከፍታው ልክ እንዲከበር መደረጉንና የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ድሉን በሚመጥን መልኩ መገንባቱን ገልጸዋል።
ልዩነቶች ቢኖሩም ለሀገር በጋራ መቆም ከዓድዋ የምንማረው ትልቅ ትምህርት መሆኑን ጠቅሰው፤ ወጣቶች የሀገርን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በእልህና በቁጭት መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የሀገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥና ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር እንደ ዓድዋ በጋራ መቆም እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መመሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን፣ የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ሕዝብ ኩራት መሆኑን ገልጸዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዓድዋ መንፈስ በርካታ ፈተናዎችን አልፎ ኢትዮጵያን ለዛሬው ቀን ማብቃቱን ጠቁመዋል።
ሠራዊቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ መገንባቱን የገለጹት ጄኔራሉ፤ ወጣቶች የሀገር ፍቅራቸውን ሠራዊቱን በመቀላቀል እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው፣ የዓድዋ ድል የ"ይቻላል" መንፈስ መገለጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት በጋራ ለመቆም ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠው፤ ከፋፋይ ሐሳቦችን በማስወገድ የተጀመሩ ትልልቅ የልማት ኢኒሼቲቮችን ለማጠናከር እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
የዓድዋን የድል መንፈስ በመላበስ ለቀጣይ የሀገር ስኬቶች ወይንም ለነገው ዓድዋ እንደሚነሱ ቃል ገብተዋል።
የዘንድሮው130ኛው የዓድዋ ድል በዓል "አኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሐሳብ ይከበራል።