ቀጥታ፡

ፈተናዋን የተሻገረች ተስፈኛ ሴት ማፍሪያ ማዕከል የሆነው - ለነገዋ

ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በተለያየ የሙያ መስክ ያሰለጠናቸውን የአራተኛ ዙር ሰልጣኞች አስመርቋል።

በመርሃግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ወጣት ቤተልሄም በቀለ የአባቷ ህይወት ማለፍ እንዲሁም የእናቷ አቅም ማጣት ከኑሮ ጫና ጋር ተደማምሮ ትምህርቷን ጨርሳ ወደ ስራ እንድትሰማራ አላስቻላትም።


 

ግራ በገባት ጊዜ መንገዷን ሊያቀና ነገዋን ሊያሰምር የሚችለውን መስመር ስትሻ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልን አገኘች።

በማዕከሉ በፋሽን ዲዛይን በመሰልጠንም በዛሬው እለት የእጅ ስራዋ በሆነው ጥበብ ደምቃ ለምረቃ በቅታለች።

በቀሰመችው እውቀትና ክህሎት ተግታ ነገ ላይ የተሻለ ሆኖ መገኘትን እንደምትፈልግና ለዚህም ውጥን መሰነቋን ገልጻ፤ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ያሉ ሴቶች ነገ የተሻለ አለና በርቱ ተስፋን ሰንቃችሁ ተጓዙ የሚል ምክርን ለግሳለች።

በዛሬው እለት ስልጠናቸውን ካጠናቀቁ ሴቶች መካከል አስቴር አለማየሁ በበኩሏ በማዕከሉ የሙያ ባለቤት ሆኛለሁ ብላለች፡፡


 

በሰለጠነችበት ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን እንደምትፈልግ በመግለጽ፤ ለዚህም ተስፋ ባለመቁረጥ በቀጣይ ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራለች።

ከዚህ ቀደም በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፋ ለዚህ መድረሷን የምትገልፀው ደግሞ ሌላዋ በማዕከሉ ሰልጥና የሙያ ባለቤት የሆነችው ነፃነት እጅጉ ነች፡፡


 

በማዕከሉ እውቀትና ክህሎት ከመገብየቷ ባለፈ ስራ በማግኘቷ ደስተኛ መሆኗንና በቀጣይም በርትታ በመስራት ለሌሎች መትረፍን የረዳትን ማህበረሰብን ማገልገል እንደምትሻም ተናግራለች።

የለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ከተማ አስተዳደሩ የሚሰራቸው ሰው ተኮር ስራዎች ማሳያ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ሂርጳሳ ጫላ(ዶ/ር) ናቸው።


 

ማዕከሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ የሚሹ ሴቶችን በማሰልጠን ወደ ስራ እንዲገቡ ማስቻሉን ጠቁመው፤ በአራተኛው ዙር ስልጠና የወሰዱ 909 ሴቶች ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል።

ሰልጣኞች የንድፈ ሃሳብና የክህሎት ስልጠና አጠናቀው የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ወስደው 97 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ማለፋቸውንም ገልጸዋል።

እስካሁኑ ባለው የስልጠና ሂደትም 2ሺህ 401 ሴቶችን ማሰልጠኑንና ሰልጣኞች የተሃድሶና የሙያ ስልጠና ማግኘታቸውን ገልፀዋል።

ማዕከሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ስነልቦናዊ ድጋፍ ለሚሹ ሴቶች የሚሰጠውን ስልጠና ለማስፋት ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም