ቀጥታ፡

አባቶች በዓድዋ ድል ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና አንድነት በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ልማት መትጋት ይገባል 

ጋምቤላ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ አባቶች በዓድዋ ድል ያሳዩትን የሀገር ፍቅርና አንድነት በማስቀጠል ለዘላቂ ሰላምና ልማት ልንተጋ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን  (ዶ/ር) ገለጹ።

ትውልዱ በዓድዋ ድል የተገኘውን የአንድነትና የመተባበር እሴት ለአገር ግንባታ ሊያውለው ይገባል

ነገ የሚከበረውን 130ኛውን  የዓድዋ  የድል መታሰቢያ በዓል በማስመልከት  የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።


 

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ህዝቦች የጀግንነትና የአንድነት ተጋድሎ ብሔራዊ ዓርማ ነው ። 

ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በዓድዋ በተባበረ ክንዳቸውና አይበገሬ ወኔያቸው የውጪ ወራሪ ኃይልን በማሸነፍ የሀገራቸውን ክብር ከፍ አድርገው ለዓለም ጥቁር ህዝቦች አሸናፊነትን ያሳዩበት ድል መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም ትውልዱ የቀደምት አባቶችን አንድነትና ፍቅር በማስቀጠል ለክልሉ ብሎም ለሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ብሔራዊ ጥቅም በአንድነትና በህብረት ሊተጋ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃሙስ ኞች በበኩላቸው፤ የዓድዋ ድል ጀግኖች አባቶች የውጪ ወራሪን በአንድነት ታግለው በማሸነፍ አኩሪ ገድላቸውን ለዓለም ማህበረሰብ ያሳዩበት ታሪካዊ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።


 

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ የአባቶቹን የድል ፍሬ በማስጠበቅ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ያለመታከት ልንሰራ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

130ኛው የዓድዋ  ድል መታሰቢያ በዓል አስመልክቶ በክልል ደረጃ በጋምቤላ ከተማ በተዘጋጀው የፓናል ውይይት  ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የክልሉ የጸጥታ አካላትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም