ትውልዱ በዓድዋ ድል የተገኘውን የአንድነትና የመተባበር እሴት ለአገር ግንባታ ሊያውለው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ በዓድዋ ድል የተገኘውን የአንድነትና የመተባበር እሴት ለአገር ግንባታ ሊያውለው ይገባል
ወልዲያ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የአሁኑ ትውልድ በዓድዋ ድል የተገኘውን የአንድነትና የመተባበር እሴት ለአገር ግንባታ ሊያውለው እንደሚገባ ተመላከተ።
በወልዲያ ከተማ "ዓድዋ ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ" በሚል መሪ ሃሳብ ከከተማዋ ወጣቶች ጋር ዛሬ ውይይት ተካሄዷል።
የዓድዋ ድል ለሀገራዊ ማንሰራራትና ለዘመናዊ አርበኝነት ስንቅ ነው
የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ፤ የጥንት አባቶቻችን አገራችንን ሊወር የመጣውን ቅኝ ገዢ ዓለምን ባስደመመ የጀግንነት ወኔ ድባቅ በመምታት ነጻነታቸውን አስከብረዋል ብለዋል።
ይህ የጀግንነት ተጋድሎ ለመላው ዓለም ጥቁር ህዝብ የነጻነት ጮራ የፈነጠቀና የኢትዮጵያውያንን አልደፈርም ባይነት ያስመሰከረ ታላቅ ገድል መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣቱ የዚያ ዘመን የኢትዮጵያ ጀግኖች በዓድዋ ተራሮች ላይ የፈጸሙትን ጀብዱ በመዘከር አደራውን ተረክቦ ለዛሬ አገር ግንባታና ለነገ ከፍታ በአንድነትና በመተባበር በመነሳሳት ሊተጋ እንደሚገባም አስረድተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ኃይሉ ታመነ በሰጠው አስተያየት፤ የዓድዋ በዓል መታሰቢያን ስናከብር ለብሔራዊ አንድነታችን ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ቃል በመግባት ነው ብሏል።
ዘመናዊ መሳሪያን ታጥቆ የመጣን ኃይል የመከቱና ያሳፈሩ አባቶቻችን ታሪክን ማውሳት ብቻ ሳይሆን እኛም ለአገራችን በተለያዩ የልማት መስኮች አዲስ ታሪክ ማስመዝገብ ይጠበቅብናል ነው ያለው።
የውስጥ ሰላምን በመጠበቅ ማፅናትና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የድርሻን መወጣት ከዚህ ዘመን ወጣት ይጠበቃል ያለው ደግሞ ሌላው የውይይት ተሳታፊ ወጣት አሰፌ ታረቀ ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ከዓድዋ ድል የምንወርሰው የጦር ሜዳ ጀብዱን ብቻ ሳይሆን በመከባበር ላይ የተመሰረተ የህዝብ አንድነትን፣ ይቅር ባይነትንና ጽናትን መሆን አለበት ብሏል።