ቀጥታ፡

የኢንቨስትመንት ማበረታቻው ፈጥነን ወደ ማምረት እንድንሸጋገር አስችሎናል- ባለሃብቶች

ጎንደር ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የኢንቨስትመንት ማበረታቻው ከቀረጥ ነጻ ማሽነሪዎችን በማስገባት ፈጥነን ወደ ማምረት እንድንሸጋገር አስችሎናል ሲሉ በማእከላዊ ጎንደር ዞን በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጹ፡፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 27 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ሥራ ገብተዋል

"ኢትዮጵያ ታምርት እኛም እንሸምት" በሚል መሪ ሃሳብ ዞናዊ የኢትዮጵያ ታምርት የንቅናቄ ማጠቃለያ መድረክ በጎንደር ከተማ ዛሬ ተካሄዷል።

የአይቤክስ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ ተወካይ አቶ ሰለሞን ዘለቀ እንደገለጹት፤ ፋብሪካውን በ160 ሚሊዮን ብር ወጪ የታሸገ ውሃ ማምረቻ ፋብሪካ በመገንባት ወደ ስራ ገብቷል።


 

ከቀረጥ ነጻ ባስገባቸው ማሽነሪዎች በመታገዝም አሁን ላይ በሰዓት 9 ሺህ እሽግ ባለ ግማሽ ሊትር ውሃ በማምረት ለገበያ ማቅረብ መጀመሩን ገልጸዋል።

ፋብሪካው አሁን ላይ ከ50 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቁመው መንግስት ያደረገው የማበረታቻ ስርዓት ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ማስቻሉን አስረድተዋል።

የአሀዱ ቢዝነስ ግሩፕ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ብርሃኑ ባዩህ በበኩላቸው፤ በተመቻቸላቸው የማበረታቻ ስርዓት ማሽነሪዎችን ከቀረጥ ነጻ ወደ ሀገር ውስጥ አስገብተዋል።


 

በ112 ሚሊዮን ብር ወጪ ያቋቋሙት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካም አሁን ላይ ሰሊጥና አኩሪ አተርን በማበጠርና በማሸግ ለአለም ገበያ ማቅረብ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው በዓመት እስከ 290 ሺህ ኩንታል የግብርና ምርቶችን ከአርሶ አደሩ በመረከብ በግብዓትነት የሚጠቀም ሲሆን በቀጣይ በምግብ ዘይት ማምረት ላይ ለመሰማራት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል። 

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ የአብስራ እሸቴ፤ በዞኑ 26 አምራች ኢንዱስትሪዎች በማበረታቻ ስርዓቱ ከቀረፅ ነጻ ማሽነሪዎችን እንዲያስገቡ ተደርጓል።


 

በተጨማሪም የመንገድ፣ የውሃና የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት እንዲሁም የብድርና የመሬት አቅርቦትን በማሳለጥ ፈጥነው ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ ሰባት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ላስመዘገቡ 76 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን አስረድተዋል።

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ በበኩላቸው፤ በዞን አሁን ላይ የሰፈነው  ሰላም ለኢንቨንስትመንት ዘርፉ መነቃቃት አስችሏል ብለዋል።


 

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ባየ አለባቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት አስችሏል።


 

በዘርፉ በስራ እድል ፈጠራ፣ ተኪና ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ምርቶችን በማምረት የውጪ ምንዛሬ ግኝትን በማስፋትና በማዳን ላይ በማተኮር እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በማጠቃለያ መድረኩ ላይ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም