ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 27 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ሥራ ገብተዋል

ጎንደር፤ የካቲት 21/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 27 አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ሥራ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታወቀ። 

አሀዱ ቢዝነስ ግሩፕ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በ112 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያቋቋመው የቅባት እህሎች ማበጠሪያና ማቀናበሪያ ፋብሪካ ተመርቋል። 


 

በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ የመምሪያው ሃላፊ አቶ የአብስራ እሸቴ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በዞኑ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመፍታት በሙሉ አቅማቸው ወደ ማምረት ሥራ እንዲሸጋገሩ እየተደረገ ነው።  

ንቅናቄውን ተከትሎ 27 ኢንዱስትሪዎች ወደማምረት ሥራ መግባታቸውን ገልጸው ባለፉት ስባት ወራት ብቻ በምግብ ዘይት፣ በጨርቃ ጨርቅና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ሰባት አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል። 


 

አምራች ኢንዱስትሪዎቹ የማምረቻ ማሽኖችን ከውጪ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ጀምሮ ከ189 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዲያገኙ መደረጉን ጠቁመዋል።

ወደ ምርት ሥራ የገቡት አምራች ኢንዱስሪዎችም ከ300 በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ እድል መፍጠራቸውንም ነው አቶ የአብስራ የገለጹት።

በዓመቱ እስካሁን ድረስ 7 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ላስመዘገቡ 76 ባለሀብቶችም የኢንቨስትመንት ፈቃድ መሰጠቱን ተናግረዋል። 

ፈቃድ የተሰጣቸው ኢንቨስትመንቶች ወደማመረት ሲሸጋገሩ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም ገልጸዋል። 


 

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አወቀ አስፈሬ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ በመደረጉ ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል እየተፈጠረ ነወ።  

ዞኑ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በጥሬ እቃነት ሊውሉ የሚችሉ የቅባትና የጥራጥሬ ሰብሎች በስፋት የሚመረትበት አካባቢ መሆኑንም አስረድተዋል።   

የአሀዱ ቢዝነስ ግሩፕ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሀኑ ባዩህ ፋብሪካው በ112 ሚሊዮን ብር ካፒታል መቋቋሙን ገልጸዋል።


 

በቀን 800 ኩንታል ሰሊጥና አኩሪ አተር አቀናብሮና አሽጎ ለዓለም ገበያ የማቅረብ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በፋብሪካው ለ20 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመው፣ በቀጣይም የምግብ ዘይት ማምረቻ ፋብሪካ በመክፈት ከውጪ የሚገባን ዘይት ለመተካት መታቀዱን ተናግረዋል። 

ፋብሪካው በዓመት ከ290 ሺህ ኩንታል በላይ ሰሊጥና አኩሪ አተር በግብአትነት እንደሚጠቀም ገልጸው፣ ይህም ለአምራች አርሶ አደሮች ሰፊው የገበያ እድል የሚፈጥር ነው ብለዋል ።

በፋብሪካው የምረቃ ሥነስርዓት ላይ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው ባለሀብቶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም