ቀጥታ፡

የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በስኬታማነት ለማስቀጠል የሁሉም አካላት ሚናና ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል 

ጭሮ ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በስኬታማነት ለማስቀጠል የሁሉም አካላት ሚናና ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ መምህራን አመለከቱ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ላለፉት ዓመታት በተለያዩ ክልሎች አጀንዳ በማሰባሰብ ምክክር ሲያካሄድ መቆየቱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቀጣይ ስምንት ወራት ዐበይት የትኩረት ጉዳዮች

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉ የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ መምህራን እንደገለጹት፤ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ ሁሉም ለውጤታማነቱ የሚጠበቅበትን ሊወጣ ይገባል።

በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪና መምህር ፈቃዱ ወርቁ እንዳሉት፤ ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ ሀገሪቱን ወደ ኃላ የጎተቱ አለመግባባቶችን ለማስወገድ ሁነኛ መፍትሄ ነው።


 

በኢትዮጵያ የሐሳብ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በምክክርና በንግግር ብቻ የመፍታት ባህልን በመቅረፅ ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ የምክክር ኮሚሽኑ ዘላቂ መፍትሄን ያመጣል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ምሁራን በጥናትና ምርምር የተደገፈና ምክንያታዊ ሀሳቦችን በማካፈል ጫፍ የወጡ አመለካከቶችን ወደ መሐል በማምጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው አመልክተዋል።ሁሉም በሚችለው አቅም ሚናውን ማጠናከር አለበትም ብለዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በንግግር እና በውይይት በመፍታት ተምሳሌት የምትሆን ሀገር ለመፍጠር እንደሚረዳ የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የፍልስፍና መምህር ድርብ ገረመው ናቸው።


 

የምክክር ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን በማገዝ እና በቀጣይ በሚካሄደው የምክክር ጉባኤ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች በንቃት እንዲሳተፉ መስራት እንደሚገባም አብራርተዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ይዞት የተነሳው ዓላማ ሰላማዊ የልዩነት እና አለመግባባት መፍቻ ዘዴ በመሆኑ ከተሸናፊነት ፉክክር የፀዳ የጋራ አገር ለመገንባት የሚጠቅም መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም