በሀገሪቱ የተዘረጋው ጠንካራ የጤና ሥርአት ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት አስችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በሀገሪቱ የተዘረጋው ጠንካራ የጤና ሥርአት ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት አስችሏል
ሀዋሳ፤የካቲት 21/2018 (ኢዜአ):-በሀገሪቱ የተዘረጋው ጠንካራ የጤና ሥርአት ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ማስቻሉን የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ሳህረላህ አብዱላሂ ገለጹ።
በሲዳማ ክልል የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል በተደረገ ጥረት አስተዋጾ ላደረጉ አካላት የእውቅናና የምስጋና ሥነስርአት ተካሂዷል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላህ አብዱላሂ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በሀገሪቱ የተዘረጋው ጠንካራ የጤና ሥርአት በተለይ ለድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም ለመገንባት አስችሏል።
ለአብነትም የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በተደመረና በተባበረ አቅም ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው የገለጹት።
በሽታውን ለመቆጣጠር በጂንካና በሃዋሳ ከተሞች የላቦራቶሪ ማዕከል በማቋቋም የመመርመር አቅምን በማሳደግና ባለሙያዎችን በማሰልጠን በቅንጅት በተሰሩ ሥራዎች ወረርሽኙን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
በሂደቱ የነበረው ቅንጅታዊ አሰራር ለተገኘው ውጤት ጉልህ ሚና እንደነበረው አስታውሰው፣ ለውጤቱ ድርሻ የነበራቸውን አካላትን አመስግነዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የማርበርግ በሽታ በሃዋሳ ከተማም መከሰቱን ተከትሎ የክልሉ መንግስት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በትብብር ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በዚህም በሽታውን ለመቆጣጣር እንደተቻለ ገልጸው፣ በሀገሪቱ ጠንካራ የጤና ስርአት መገንባቱ እና በክልሉም የጤና ባለሙያዎች፣ አጋር ድርጅቶችና ማህበረሰቡ በቅንጅት መስራታቸው ለውጤት አብቅቷል ብለዋል።
በሀገሪቱ ጠንካራ የወረርሽኝ መከላከልና ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመቆጣጠር አስችሏል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሃይሉ ናቸው።
በተለይ የተቀናጀና ውጤታማ የቅኝት ስርዓት በመኖሩ በሽታውን በአጭር ጊዜ መቆጣጠር እንደተቻለ ገልጸው፣ በሲዳማ ክልል የታየው የአመራር ቁርጠኝነትም ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብለዋል፡፡
ከኮቪድ ወረርሽን የተገኘው ተሞክሮ ማርበርግን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አዎንታዊ አስተዋጾ ማድረጉን የተናገሩት ደግሞ የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሰላማዊት መንገሻ ናቸው።
በተለይም በቅድመ ዝግጅት ሥራ በክልሎች የላቦራቶሪ አቅም እንዲያድግ መደረጉ ውጤት ያስገኘና በሀገሪቱ ጤና ስርዓት ለውጥ ያመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ የማርበርግ ቫይረስ በሽታን በመከላከል ሂደት የተከናወኑ ተግባራት ለተሞክሮ የቀረቡ ሲሆን በሽታው በቁጥጥር ስር እንዲውል አስተዋጽኦ ያበረከቱ የጤና ተቋማት፣ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ምስጋናና እውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በወርሃ ጥቅምት ተከስቶ የነበረውን የማርበርግ ቫይረስ በሽታን ለመከላከል ኢትዮጵያ በወሰደችው የተቀናጀና አስቸኳይ ምላሽ ቫይረሱን ከኢትዮጵያ ማጥፋት እንደተቻለ ጤና ሚኒስቴር ከአንድ ወር በፊት ማስታወቁ የሚታወስ ነው።