የትውልዱ ዓድዋ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ድህነትን ማሸነፍ ሊሆን ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የትውልዱ ዓድዋ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ድህነትን ማሸነፍ ሊሆን ይገባል
ሆሳዕና ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ የትውልዱ ዓድዋ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ድህነትን ማሸነፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ፡፡
የዓድዋ ጀግኖችን ፈለግ በመከተል የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት፣ የድል ብስራትና የአሸናፊነት ምልክት መሆኑ ታሪክ የመዘገበው ሃቅ ነው።
የዓድዋ ጦርነት ትልቁ የጀግንነት መገለጫ ኢትዮጵያውያን ከዳር ዳር ተሰባስበው ለሀገራቸው አንድ ዓላማ ሰንቀው፤ የአሸናፊነት እልህ ታጥቀው ጠላትን ገጥመው ማሸነፍ መቻላቸው ነው።
ከዚህ የድል ብስራትና ደማቅ የታሪክ ምእራፍ የአሁኑ ትውልድ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን፣ ጀግንነትን፣ ለሀገር ክብር በጋራ መቆምን ሊማር እንደሚገባ ምሁራን ይናገራሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሳምሶን ወልዴ፤ የዓድዋ ድል ደማቅና የገዘፈ ታሪክ የተፃፈበት የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ምልክት መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም የዚህ ትውልድ ዓድዋ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር፣ ልማትን ማረጋገጥና ድህነትን ማሸነፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያዊያን የውስጥ አንድነትን አጠናክረን ለሀገር ልማትና ብልጽግና በጋራ መስራት የግድ የሚልብን ወሳኝ ምእራፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና ተመራማሪ አበራ ሄቢሶ፤ የዓደዋ ድል የቀደሙት አያቶች ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት በአንድነት ዘምተው ድል ያደረጉበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በመሆኑም በዚህ ዘመንም በሀገር ጉዳይ ያለልዩነት በጋራ መቆም እንደሚገባ ትውልዱ የሚማርበት መሆኑን ገልጸው በልማትና ምርታማነት ከተረጂነት በመውጣት የሀገርን ክብር የምናስጠብቅበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በነገው እለት በድምቀት ይከበራል።