የዓድዋ ጀግኖችን ፈለግ በመከተል የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ጀግኖችን ፈለግ በመከተል የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፡- የዓድዋ ጀግኖችን የድል ፈለግ በመከተል የሀገርን ጥቅም ማስጠበቅና ዕድገቷን ማስቀጠል አለብን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
ወጣት ዮሴፍ አበራ ለኢዜአ እንዳለው፤ አያቶቻችን በዓድዋ ጦርነት መስዋዕትነትን ከፍለው ሉዓላዊነቷ የተረጋገጠ ሀገር አስረክበውን አልፈዋል።
ስለዚህ ከድሉ ወጣቶች ብዙ ትምህርት በመውሰድ በሀገራዊ ልማት ዐሻራችንን በማሳረፍ በላባችን የሀገርን ክብር ማፅናት ይጠበቅብናል ሲል በአጽንኦት ገልጿል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ማርቆስ እሸቱ፤ አሁን ያለነው ትውልድ የምናልመውን ስኬት ለመጎናፀፍ ከዓድዋ ድል የዓላማ ፅናትን ልንማር ይገባናል ብሏል።
ሀገሪቱ ወደ ብልፅግና የምታደርገው ጉዞ ፍሬያማ እንዲሆን ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ፣ ዋነኛ የልማት ኃይልና ዕድሎችን ወደ ተግባር የሚቀይሩ መሆን እንዳለባቸውም አስገንዝቧል።
ከ130 ዓመት በፊት አባቶቻችንን ምቹ መደላድል ባልተፈጠረበት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ዳር ድንበሯ የተጠበቀች ሀገር አስረክበውናል፤ እኛ ደግሞ በተሰማራንበት የሙያ መስክ የተሻለ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል ያለው ደግሞ ወጣት አሕመድ አሊ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሙህዲን ናስር ደግሞ፤ ዓድዋ ኢትዮጵያውያንን የብሔር፣ የሐይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይገድባቸው ለአንድ ዓላማ ያስተባበረ ትልቅ የድል ታሪክ መሆኑን አንስቷል።
በአሁኑ ዘመንም ወጣቶች በአንድነት ለሀገር ሁለንተናዊ ብልፅግና በመቆም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ለልማት በጋራ በመቆም ሀገራዊ ግዴታችንን መወጣት አለብን ሲል ጥሪውን አቅርቧል።