ወጣቶች ከዓድዋ አባቶች የወረሱትን የአይበገሬነት እሴት በልማት መድገም ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች ከዓድዋ አባቶች የወረሱትን የአይበገሬነት እሴት በልማት መድገም ይጠበቅባቸዋል
ደብረ ብርሃን ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ ትውልዱ የዓድዋን እሴት በመውረስ በኢትዮጵያ ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥና የራሱን ታሪክ በደማቁ ሊጽፍ እንደሚገባ የሰሜን ሸዋ ዞን አርበኞች ማህበር አስታወቀ።
የዓድዋ ድል ለአፍሪካዊያን የጋራ ደኅንነትና ወታደራዊ ትብብር ትልቅ መሠረት ነው
የሰሜን ሸዋ ዞን ጀግኖች አርበኞች ማህበሩ ሊቀመንበር ተክለስላሴ ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት፣የዓድዋ ድል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ያረጋገጠ ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት ነው።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ወጣቱ ትውልድ ይህንን የአንድነትና የአይበገሬነት መንፈስ ወደ ልማት አርበኝነት በመቀየር ሀገራዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።
አሁን ላይ የሚጠይቀው የሰላም ብሎም የልማት አርበኝነት ድህነትን ማሸነፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ወጣቱ በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ የሃገር ባለውለታነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል ብለዋል።
ሌላው የማህበሩ አባል ዮሃንስ ተሰማ የድሉን ታሪክ ለትውልድ ማሸጋገር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወጣቱ የሀገሪቱን ዕድገት በማይመኙ ኃይሎች ሴራ ሳይጠለፍ፣ የሰላምና የአንድነት እሴቶችን ጠብቆ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የዓድዋ ድል በዓል ሲከበር የሀገራችንን ሉዓላዊነት በመጠበቅ፣ ሰላምን በማጽናት እና የተጀመሩ የልማት ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪ ጌጤ መንግስቱ ናቸው።
በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የቅርስ ጥበቃ ቡድን መሪ አክሊል ጌታቸው፤ ወጣቱ ከዓድዋ እሴት መቻቻልንና ለሀገር ክብር በጋራ መቆምን መማር አለበት ብለዋል።
ትውልዱ አሁን ላይ በጋራ በመቆም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፎች መዘጋጀትና መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።