ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

አርሰናል እና ቼልሲ ዛሬ የሚያደርጉት የሊግ ጨዋታ ይጠበቃል



በዚህም መሠረት ከቀኑ 7 ሰዓት ቦሌ ክፍለ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 15 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል። በአምስት ጨዋታዎች ላይ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ 17 ግቦችን ሲያስቆጥር  13 ጎሎችን አስተናግዷል።

ቦሌ ክፍለ ከተማ በ26 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

ተጋጣሚው ይርጋጨፌ ቡና በውድድር ዓመቱ 15 ጨዋታዎችን አከናውኖ በሁለቱ ድል ሲቀናው ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። ሰባት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 20 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በ11 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ጨዋታው ቦሌ ክፍለ ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፤ ይርጋጨፌ ቡና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።

በሌላኛው መርሐ-ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከልደታ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአበባ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ድሬዳዋ ከተማ እስከ አሁን በሊጉ 15 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፤ ስድስት ጨዋታዎችን ሲያሸንፍ ስምንት ጊዜ ተሸንፏል።

በአንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል። በ15ቱ ጨዋታዎች ላይ 15 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 22 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ19 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።

ልደታ ክፍለ ከተማ በሊጉ 15 ጨዋታዎችን አድርጎ በሶስቱ ሲያሸንፍ 10 ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 15 ግቦችን ሲያስቆጥር 28 ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ11 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱም ቡድኖች ተከታታይ የሊግ ድላቸውን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 16ኛ ሳምንት እስከ የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሊጉን በ40 ነጥብ እየመራ ነው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ38 ነጥብ ይከተላል።

የኢትዮ ኤሌክትሪኳ ዳግማዊት ሰለሞን በ18 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራች ነው።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በ12 ግቦች ቀጣዩን ደረጃ ይዛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም