ቀጥታ፡

አርሰናል እና ቼልሲ ዛሬ የሚያደርጉት የሊግ ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 22/2018 (ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ28ኛ ሳምንት መርሐ ግብር አርሰናል እና ቼልሲ የሚያከናውኑት ጨዋታ የእግር ኳስ ቤተሰቡን ትኩረት ስቧል።



ጨዋታው ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።

አርሰናል በሊጉ ካካሄዳቸው 28 ጨዋታዎች መካከል 18 ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።



መድፈኞቹ በጨዋታዎቹ 56 ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፉ 21 ግቦች ተቆጥሮባቸዋል።

በ43 ዓመቱ ስፔናዊ ማይክል አርቴታ የሚሰለጥነው አርሰናል በ61 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ቼልሲ በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው 27 ጨዋታዎች 12 ጊዜ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ተሸንፎ በዘጠኝ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል።

ሰማያዊዎቹ በጨዋታዎቹ 48 ግቦቹን ሲያስቆጥሩ 31 ጎሎችን አስተናግደዋል።

በ41 ዓመቱ እንግሊዛዊ ሊያም ሮሲኒየር የሚመራው ቼልሲ በ45 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።

ሁለቱ ክለቦች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የዛሬው ለ214ኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም በነበራቸው 213 የእርስ በእርስ ግንኙነቶች አርሰናል 86 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ቼልሲ በ66ቱ አሸንፎ በ62 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ወጥተዋል።

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ባደረጓቸው 67 ጨዋታዎች አርሰናል 27 ጊዜ ሲያሸንፍ ቼልሲ 20 ጊዜ አሸንፏል። 20 ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ክለቦቹ ባደረጓቸው ያለፉት 10 የሊግ ጨዋታዎች መካከል አርሰናል ስድስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ቼልሲ አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ተለያይተዋል።

አርሰናል እና ቼልሲ በለንደን ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ተቀናቃኝ ቡድኖች ናቸው። ለ119 ዓመታት የዘለቀ ፉክክር አድርገዋል።

አርሰናል የሊጉን ዋንጫ 13 ጊዜ ሲያነሳ ቼልሲ 6 ጊዜ የዋንጫው ባለቤት ሆኗል።

መድፈኞቹ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፉ ከተከታዩ ማንችስተር ሲቲ ጋር ያላችውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ከፍ ያደርጋሉ።

ለቼልሲ በሻምፒዮንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚያደርገው ፉክክር ሶስት ነጥብ ማግኘት ወሳኝ ነው።

የ40 ዓመቱ ዳረን ኢንግላንድ ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።


 

በሌሎች መርሐ ግብሮች ማንችስተር ዩናይትድ ከክሪስታል ፓላስ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ በሰልኸረስት ፓርክ  ይጫወታሉ።

ብራይተን ከኖቲንግሃም ፎረስት፣ ፉልሃም ከቶተንሃም ሆትስፐርስ በተመሳሳይ ከቀኑ 11 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም