7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው - ኢዜአ አማርኛ
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
የኢዜማ፣ የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአብን ፓርቲ አመራሮች ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሁሉንም አካላት ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ምክትል መሪ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን እንዳሉት፥ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የምርጫው ሂደት ስኬታማነት ወሳኝ ነው።
በሂደቱም መራጩ ሕዝብ፣ ገዥው ፓርቲ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ተቋማት፣ ምርጫ ቦርድና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የየራሳቸው የጋራና የተናጠል ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
ትልቁ ዓላማችን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሆን አለበት ያሉት አርክቴክት ዮሐንስ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካልና ዜጋ ሕግን በማክበር ሀገራዊ ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበር አበራ በቀለ በበኩላቸው የዘንድሮው ምርጫ ለኢትዮጵያ የተረጋጋ ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ ጉዞ ጠንካራ መሠረት የምናኖርበት ነው ብለዋል።
በምርጫው የሚያሸንፍ ሐሳብ ይዘን እንቀርባለን ያሉት አቶ አበራ ምርጫው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዲሞክራሲ ምዕራፍ የሚያሻግር ወሳኝ የታሪክ አጋጣሚ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) የሥራ አስፈጻሚ አባል የሱፍ ኢብራሂም፥ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር በዲሞክራሲያዊ ምርጫና በሀሳብ የበላይነት ብቻ መሆን እንዳለበት ፓርቲያቸው በጽኑ እንደሚያምን ገልጸዋል።
ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እጅግ ሰፊ ዝግጅትን የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ከማኒፌስቶ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ አማራጭ ሐሳብን የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚጠይቅ አስረድተዋል።
ምርጫ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ አካል በመሆኑ፥ ፓርቲያቸው ለሀገር ወሳኝ በሆነው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጉን አስታውቀዋል።