ቀጥታ፡

የሆርቲካልቸር ልማትን በማዘመን የወጪ ንግድ ገቢን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቷል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦የሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍን በማዘመን ከዘርፉ የወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ የበለጠ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የሆርቲካልቸር ምርቶች ከ288 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

የግብርና ሚኒስቴር በሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት የ2018 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የኤክስፖርት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።


 

በግምገማው ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ እንደገለጹት፤ ባለፉት ሰባት ወራት ከአበባ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የወጪ ንግድ ከ288 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። 

ይህም ውጤት በዘርፉ የታየውን አበረታች መሻሻል የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት በማውጣት በመስኖና በቴክኖሎጂ ለማዘመን በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ይህም ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የአበባ ልማት እርሻን አሁን ካለበት 1 ሺህ 400 ሄክታር ወደ 3 ሺህ ሄክታር መሬት ለማስፋት የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

ግብርናው የሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ እንዲቀጥልና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


 

በሆርቲካልቸር ልማት የተሰማሩ የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የማስፋፊያ ቦታ፣ የመሠረተ ልማትና ሌሎች ችግሮች እንዲቀረፉላቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ በበኩላቸው፥ በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት ከሚኒስቴሩ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የዛሬው መድረክም ለባለሀብቶች አስቻይ ሁኔታን በመፍጠር ረገድ ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ በሰጡት ማጠቃለያ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን ለመፍታትና ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ለመፍጠር መንግስት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የመሬት፣ የመሠረተ ልማትና የፋይናንስ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሠራ አጽንኦት ሰጥተዋል።

መሬት ወስደው ሳያለሙ ለረጅም ዓመታት ባስቀመጡ ባለሀብቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያነሱት።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለአምራች ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰው፥ ለላቀ ውጤታማነት መረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም