ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የሆርቲካልቸር ምርቶች ከ288 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የሆርቲካልቸር ምርቶች ከ288 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ ባለፉት ሰባት ወራት ወደ ውጪ ከተላኩ የሆርቲካልቸር ምርቶች ከ288 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ ገለጹ።
ግብርና ሚኒስቴር በሆርቲካልቸር ኢንቨስትመንት የ2018 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የኤክስፖርት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
በዚሁ ወቅት ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ እንዳሉት በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ሰባት ወራት ከሆርቲካልቸር ምርቶች የወጪ ንግድ ከ288 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል።
ገቢው ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላኩ የአበባ እንዲሁም አትክልት እና ፍራፍሬ ምርቶች የተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግና ጥራትን በማስጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሳደግ እየሠራ እንደሚገኝ አንስተዋል።
የግብርና ልማትን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፣ ዘመናዊ የእርሻ ልማት ስራዎችን የማስፋፋት ስራዎችን የበለጠ ውጤታማ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።
በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ባለሀብቶች የሚገጥማቸውን ችግሮች በመቅረፍ የተሻለ ስኬት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።