ቀጥታ፡

በአካባቢያችን በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ ሆነናል-የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች

ነቀምት ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦በምስራቅ ወለጋ ዞን የሰፈነውን ሰላም ተከትሎ በአካባቢያቸው በተከናወኑ የልማት ሥራዎች ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን የዞኑ ነዋሪዎች ገለጹ። 

በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ከምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ጋር በሰላም እሴት ግንባታ ላይ በነቀምቴ ከተማ መክሯል።

በመድረኩ ላይ የተገኙ የዞኑ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት በዞኑ በነበረው የሰላም እጦት ለእንግልትና ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገው ቆይተዋል።


 

መንግስት የአካባቢውን ሰላም ለመመለስ በቁርጠኝነት ባከናወናቸው ተግባራት በአሁኑ ወቅት ሰላም መስፈኑንና በዚህም የልማት ሥራዎች በመፋጠናቸው ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ነዋሪ አቶ ፈዬራ ስጦታው፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሰላም እጦት ለጉዳት ሲዳረጉ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ጉቶ ጊዳን ጨምሮ በተለያዩ የዞኑ ወረዳዎች ሰላም ሰፍኗል ብለዋል።

በዚህም በዞኑ የልማት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ የልማት ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠል ከመንግስት ጎን በመሆን ለዘላቂ ሰላም ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። 


 

የሰላም ሥራ ለፀጥታ አካላት ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁላችንንም ተሳትፎና ርብርብ ይፈልጋል ያሉት ደግሞ አቶ ብዙአየሁ ኬነሳ የተባሉ  የሌቃ ዱለቻ ወረዳ  ነዋሪ ናቸው።

በየአካባቢው የልማት ሥራን ማፋጠንና ከዚያም ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ሰላም ሲኖር እንደሆነ በማየታችን ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን ብለዋል።

በአካባቢያቸው ሰላም በመስፈኑ ማህበረሰቡ ከምንጊዜውም በላይ ፊቱን ወደ ልማት መመለሱንም ተናግረዋል።

የሳሲጋ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ታደለ ታደስ በበኩሉ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት የወረዳው ነዋሪዎች በተለያዩ ጽንፈኛ ታጣቂዎች ምክንያት ለመፈናቀል፣ ለሞት፣ ለንብረት ዝርፊያና ሌሎች ችግሮች ይዳረጉ እንደነበር አስታውሷል።

ይሁንና በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በአሁኑ ወቅት በአካባቢያቸው ሰላም መረጋገጡን ገልጾ፣ መተንፈስ የጀመርነውን የሰላም አየር ለማስቀጠል ሌትተቀን እንሰራለን ብሏል።

ትምህርት ቤት፣ ባንክና ሌሎች የመንግስት ተቋማት ወደ ስራ መመለሳቸው ለነዋሪው እፎይታ ማስገኘቱንም ተናግሯል።    


 

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙአየው ተክሌ፣ ሰላም ለሁሉም ነገር አስፈላጊ በመሆኑ ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም ጸንቶ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል። 

በቅንጅት ከተሰራ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል ገልጸው፣ ለዚህ እውን መሆን ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር ሆኖ የጀመረውን የሰላምና ጸጥታ ሥራ ማጠናከር አለበት ብለዋል። 

መድረኩም ማህበረሰቡ ለሰላም እሴት ግንባታ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ለሜሳ ኦልጂራ በበኩላቸው ሰላም አስፈላጊ መሆኑን  ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአካባቢው የተከሰተውን ችግር ብቻ ማስታወስ በቂ ነው ብለዋል። 

አሁን በአካባቢው የሰፈነው ሰላም  በዞኑ ሰፋፊ የልማት ሥራዎችን ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረ ኮሎኔል ለሜሳ ገልጸው፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከተከናወኑ የልማት ሥራዎች መካከል የነቀምት የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የነቀምቴ-ኡኬ አስፓልት መንገድ፣ ፋብሪካዎች፣ የመስኖ ፕሮጀክቶችና ትምህርት ቤቶችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

እነዚህን የልማት ስኬቶች ለማስቀጠል እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የህብረተሰቡ ሚና ወሳኝ በመሆኑ ህዝቡ በየደረጃው ከሚገኙ የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የአካባቢውን ሰላም እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም