በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ ከተማ አስተዳደር በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወጪ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ ነው
ነቀምት፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ)፡-በኦሮሚያ ክልል በነቀምት ከተማ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ መመለስ የሚያስችሉ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የነቀምቴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተመስገን ምሬሳ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በበጀት ዓመቱ 16 አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።
በበጀት ዓመቱ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የኮሪደር ልማት፣ የአንድ መሶብ አገልግሎት መስጫ ማእከል ህንፃ፣ የውስጥ ለውስጥ የጎርፍ መፋሰሻ ቱቦዎች ቁፋሮና ጥገና ሥራ ይገኙበታል ብለዋል።
እንዲሁም ለስራ እድል ፈጠራ የሚያገለግሉ ምርጥ ዘርያ ያላቸው ዶሮ መፈልፈያ ሼዶች፣ የአሳ ማራቢያ ገንዳዎች እና ሌሎችም የልማት ስራዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
በተለይ የአንድ መሶብ አገልግሎት ህንፃ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት ሲጀምር የመልካም አስተዳደር ቅሬታዎችን ለመፍታት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በኮሪደር ልማት ስራም 8 ኪሎ ሜትር በላይ የአስፓልት መንገድ ዝርጋታ፣ የወለጋ ሙዚየም ግንባታ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የሳይክል መጋለቢያ፣ የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎች እና የንግድ ቤቶች ስራ እንደሚያካትት አመላክተዋል።
በልማት ፕሮጀክቶቹ ግንባታም በርካታ የከተማዋ ወጣቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸው ተናግረዋል።
በነቀምቴ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የኮሪደር ስራ የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባለፈ ለነዋሪዎች ምቹ መዝናኛ ስፍራ እንደሚሆን የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ጉተማ ተካልኝ በሰጡት አስተያየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ ከተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴ ውሰጥ የኮሪደር ስራ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተማን በማዘመን ለኑሮ ምቹ ለማድረግ መንግስት እንደ ሀገር የጀመረው የኮሪደር ስራ ነቀምቴንም ተጠቃሚ በማድረጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
አቶ መሸሻ ዘውዴ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የልማት ስራዎች የከተማዋን እድገት የሚያፋጥኑና የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደሚያቃልሉ ተናግረዋል።
በተለይ ፕሮጀክቶቹ የከተማዋን ወጣቶች የስራ ባህል በመቀየር ገንቢ ሚና እንዳላቸው አስታውቀዋል።
ወይዘሮ ሞቱ ደጀኔ በበኩላቸው የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ በፊት ቆሻሻ የሚጣልባቸው ቦታዎች ወደ አማረ መዝናኛ ስፍራዎች በመለወጥ የከተማዋ ገጽታን በመቀየር ውብ እያደረጋት መሆኑን አስረድተዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች እየተገነቡ መሆኑም ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።
በተለይ ለልማት ስራዎቹ ህብረተሰቡ ያሳየው ትብብር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።