ቀጥታ፡

በደብረ ማርቆስ ከተማ  የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦በደብረ ማርቆስ ከተማ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸው ተመላከተ።

በከተማዋ ወቅታዊ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ያተኮረ የወጣቶች ውይይት ተካሂዷል።

በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የወጣቶች ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል

የከተማ አስተዳደሩ ስራና ክህሎት መምሪያ ምክትል ሃላፊ ዘሪሁን ደገፍ እንዳሉት፤ በከተማዋ ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከ18 ሺ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እስካሁን ባለው ሂደት ከ12 ሺ በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል። 


 

ከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችን ከማመቻቸት ባለፈ ከ17 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ማመቻቸቱንም ተናግረዋል።

የከተማዋን ሁለንተናዊ ልማትና ዕድገት ለማረጋገጥ ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በንቃት መጠበቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ጫኔ ታደለ፤ በንብ ማነብ ዘርፍ ተሰማርቶ ውጤታማ እየሆነ መሆኑን ገልጿል።

ወጣት ምህረት መልካም በበኩሏ ሰርቶ መለወጥ የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ መንግስት ሰላምን ለማስፈን በሚያደርገው ጥረት ውስጥ የድርሻዋን እንደምትወጣ ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም