በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የወጣቶች ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የወጣቶች ተጠቃሚነት እያደገ መጥቷል
ባህርዳር፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የወጣቶች ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱ ተገለጸ።
በክልሉ በተለይም በዶሮ እርባታ የተሰማሩ ወጣቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ወጣት መሳይ ታምራት በባህር ዳር ከተማ የዶሮ ጫጩት ማሳደግ እና ማከፈልፈል ስራ ላይ በማህበር ተደራጅቶ ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት ሆኖታል።
በከተማ አስተዳደሩ በተደረገላቸው ሁለት ሼዶች ድጋፍ በአምስት ዙር የተረከቧቸውን የአንድ ቀን ጫጩቶች በማሳደግ ከ19 ሺህ በላይ ቄብ ዶሮዎችን ለአርቢዎች ማከፋፈላቸውን ገልጿል።
ከአንድ አመት በፊት በ275 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የጀመሩት ስራ አሁን ለይ በፍጥነት በማደጉ የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸወን አረጋግጧል።
በቀጣይ ጠንክረው በመስራትና በመቆጠብ የዶሮ ጫጩት ማስፈልፈያ ማሽን በመግዛት የእንቁላል ጣይና የሥጋ ዶሮዎችን በማስፈልፈል ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማሳደግ እየሰሩ መሆኑን አመልክቷል።
ወጣት ዮሴፍ ፈቃዱ በበኩሉ ሰባት ሆነው በመደራጀት በተደረገላቸው የሼድና የአንድ ቀን ጫጩት ድጋፍ ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጿል።
ከአንዳሳ የግብርናና የእንስሳት ምርምር ማእከል ተረክበው ያሳደጓቸውን ከሰባት ሺህ በላይ ቄብ ዶሮዎች በሰቆጣ፣ ጎንደርና ፍኖተሰላም አካባቢ ለሚገኙ አርቢዎች በማሰራጨት የተሻለ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግሯል።
አሁን ላይ አራት ሺህ የአንድ ቀን ጫጩቶችን ተረክበው በማሳደግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው በቀጣይ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በማርባት ተጠቃሚነታቸውን ለማስፋት እየሰሩ መሆኑን አብራርቷል።
በአማራ ክልል እንስሳትና አሳ ሃብት ልማት ቢሮ የእንስሳት ባለሙያ ሙላቱ ዳኘው እንዳሉት የሌማት ትሩፋት በዶሮ ልማት፣ በወተትና አሳ ሀብት ልማት ዘርፉ ከፍተኛ ወጤት እያስመዘገበ ነው።
በበጀት ዓመቱ 13 ሚሊየን የአንድ ቀን ዶሮ ጫጩቶችን ለአሳዳጊዎች ለማሰራጨት ታቅዶ በተደረገ ጥረት እስካሁን ከሰባት ሚሊየን በላይ ጫጩቶችን ለሶስት ሺህ 439 አሳዳጊዎች ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት 7 ወራት ከሰባት ሚሊየን በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችን ለአሳዳጊዎች ማስረከብ መቻሉንም አመልክተዋል።
የዶሮ እርባታ ዘርፍ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ዘላቂ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ እንደሚገኝም አስረድተዋል።