ቀጥታ፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የኢፋ ቦሩ 2ኛ  ጀረጃ ትምህርት ቤት ስጦታ አበረከተ

አምቦ ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦የቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በአምቦ ከተማ አስተዳደር ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በተወለዱበት ኢላሞ ጎረምቲ ወረዳ ለሚገኘው ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የኢፋ ቦሩ 2ኛ  ጀረጃ ትምህርት ቤት ስጦታ አበረከተ።

በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የጥበብ ስራዎች ውስጥ ትውልዱ ራሱን በማየት የሀገሩን አርት ለማሳደግ መትጋት አለበት

ስጦታዎቹም የተለያዩ ኮምፒዩተሮች፣ ፕሪንተሮች፣ መፅሀፍቶች፣ የሚኒ ሚዲያ ቁሳቁሶች፣ የሴት ተማሪዎች የንፅህና መጠበቂያ፣ የህክምና መሳሪያዎች እና ሌሎች ለመማር ማስተማር የሚያገለግሉ  ግብአቶች ነው።


 

የቀዳማዊት እመቤት ፅህፈት ቤት ይህን ስጦታ ያበረከተው በአምቦ ከተማ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን 20ኛ አመት የዕረፍት መታሰቢያ ፕሮግራም ላይ ነው።

ዛሬ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን  የሚያስተምረው ትምህርት ቤቱ የተገነባው በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በ2015 ዓ.ም ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመፅሀፍ ሽያጭ በተገኘ ገቢ ነው።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ)፤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክት በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስም ትምህርት ቤቱ መገንባቱ ትልቅ የታሪክ አሻራ መሆኑን አንስተው የአሁኑ ትውልድም ለጥበብ ስራዎች  የሀገሩን ጥበብ ለማሳደግ መትጋት አለበት ብለዋል።


 

የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ትምህርት ቤቱን ከማስገንባት ባለፈ፣ ለተማሪዎች የመማር ማስተማር ሂደት ግብዓት የሚሆኑ ልዩ ልዩ ድጋፎችን ማድረጉን ገልጸዋል። 

በዚህም መሠረት ለትምህርት ቤቱ አገልግሎት የሚውሉ ላፕቶፖች፣ ፕሪንተሮችና ሌሎች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን ጨምሮ በጠቅላላው 8 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ በስጦታ መልክ መበርከቱን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ ከተገኙት አርቲስቶች መካከል አርቲስት አበበ ባልቻ፤ የሎሬቱ የጥበብ ሥራዎች በርካታ አርቲስቶችን በማፍራት በሀገራችን የጥበብ እድገት ውስጥ የማይረሳ አሻራ አኑረዋል ብሏል። 


 

የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን አርአያነት በመውሰድ፣ የሀገራችንን ጥበብ አሁን ካለበት ለማሳደግ መስራት ይጠበቅብናል ብሏል። 

በመሆኑም በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስም የተሰየመው የኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ተናግሯል።

አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ፤  ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካ የጥበብ እድገት በዓለም መድረክ እንዲታይ ያደረገ ታላቅ ባለውለታ መሆኑን ገልጿል።


 

በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስም ለተሰየመው የኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በቀጣይ ሌሎች አርቲስቶችን በማስተባበር ድጋፍ እናደርጋለን በማለት አርቲስቶቹ ቃል ገብተዋል።

የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ፤ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የሀገራችንን አርት ለዓለም ያስተዋወቁ ድንቅ የሀገር ባለውለታ በመሆናቸው ታላቅ ክብር የሚገባቸው መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም በቀዳማዊት እመቤት  ዝናሽ ታያቸው ጽህፈት ቤት በሎሬቱ ስም ትምህርት ቤቱ በመገንባቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም