ቀጥታ፡

በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የጥበብ ስራዎች ውስጥ ትውልዱ ራሱን በማየት የሀገሩን አርት ለማሳደግ መትጋት አለበት

አምቦ ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የጥበብ ስራዎች ውስጥ ትውልዱ ራሱን በማየት የሀገሩን አርት ለማሳደግ መትጋት አለበት ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ገለጹ።

ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን 20ኛ ዓመት ህልፈተ ህይወት መርሃ ግብር መነሻውን በአዲስ አበባ ራስ መኮንን ድልድይ (70 ደረጃ) ከሚገኘው የሎሬቱ መታሰቢያ ሐውልት ጋር በማድረግ ወደ ሎሬቱ ትውልድ ከተማ አምቦ በማቅናት በተለያዩ ኹነቶች ተከብሯል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የኪነ-ጥበብና ስነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው የሎሬቱን የጥበብ ትሩፋትና በጎ አሻራ ለወጣቱ ትውልድ ለማስተላለፍ መሆኑንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ ራሱን በሎሬቱ የጥበብ ስራዎች ውስጥ በማየት የሀገሩን አርት ለማሳደግ ጠንክሮ መስራት አለበት ብለዋል።

ለዚህም በየዓመቱ የሎሬት ፀጋዬን የአርት ስራዎች የሚዘክርና የሚያሳዩ ስራዎችን በቋሚነት ለመስራት ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ማቀዱንም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ በበኩላቸው፤ ሎሬቱ የሀገራችንን አርት ለዓለም ያስተዋወቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።


 

ቢሮው መሰል የጥበብ ሰዎችን ለማፍራት የሚያስቸሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው ይህንንም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት አርቲስቶችም የሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህንን አርአያነት በመውሰድ፣ የሀገራችንን ጥበብ አሁን ካለበት ለማሳደግ ተባብረው እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኘው አርቲስት አበበ ባልቻ እንደገለፀው፤ የሎሬቱ የጥበብ ሥራዎች በርካታ አርቲስቶችን በማፍራት በሀገራችን የጥበብ እድገት ውስጥ የማይረሳ አሻራ አኑረዋል። 


 

አርቲስቱ አክሎም በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስም ለተሰየመው የኢፋ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ሌሎች አርቲስቶችን በማስተባበር በየዓመቱ በመምጣት አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብሏል።

ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን የኢትዮጵያን ጥበብ ከማሳደግ ባለፈ የአፍሪካ የጥበብ እድገት በዓለም መድረክ እንዲታይ ያደረገ መሆኑን የገለፀው ደግሞ አርቲስት ተፈሪ አለሙ ነው።


 

ሀገራችን ኢትዮጵያን እንድንወድ ያደረገ ታላቅ አርቲስት ነው ሲልም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም