ቀጥታ፡

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት በማስጠበቅ የአባቶቹን የዓድዋ ጀግንነት ታሪክ እያስቀጠለ ነው

ሰቆጣ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ የአባቶቹን የዓድዋ ጀግንነት ታሪክ እያስቀጠለ መሆኑን የሰራዊቱ አባላት ገለጹ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት የዓድዋን የጀግንነት ታሪክ በመድገም የሀገርን አንድነትና ዳር ድንበር የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም የተገኘ የአንድነት ውጤት ነው

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሚገኙ የሠራዊቱ አባላት ለሀገር ሉዓላዊነትና ቀጣይነት ላለው ዕድገት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጮራን የፈነጠቀ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ነው ብለዋል።


 

ከሰራዊቱ አመራሮች መካከል ሻለቃ ተክላይ አማረ፤ የዓድዋ ድል የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታና የሕዝቦች አንድነት በተግባር የታየበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሠራዊቱ ዛሬም የአባቶቹን አርበኝነት በመውረስ የሕዳሴው ግድብን በመገንባት የዳግማዊ ዓድዋን ታሪክ በደማቁ ጽፏል ብለዋል።

የዓድዋ ድል የውጭ ወራሪን ብቻ ሳይሆን የውስጥ ባንዳዎች ተልዕኮ የከሸፈበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ሠራዊቱ በአሁን ጊዜ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመፈታተን የሚሞክሩ የውስጥና የውጭ ኃይሎችን ድል የማድረግ ብቁ ቁመና ላይ ነው ብለዋል።

የ204ኛ ኮር ሻምበል አዛዥ መቶ አለቃ እንድሪስ ጀማል፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆሙ ለዓለም የሚተርፍ ታሪክ መስራት እንደሚችሉ ዓድዋ ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

ሠራዊቱ ከጀግና አባቶች የተረከባትን ሀገር ዳር ድንበሯን አስጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማስረከብና የተሰጠውን ግዳጅ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ምክትል አስር አለቃ አጥቃቸው ሙሉዬ፤ ጀግኖች አርበኞች ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ጠላት በሀገር ፍቅር ስሜት እንዳሸነፉት ሁሉ ዛሬም ሠራዊቱ ያንን ጽናት በመላበስ ማንኛውንም ተልዕኮ በብቃት ለመፈጸም ዝግጁ ነው ብለዋል።


 

ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር ልማት በትጋት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ነው ብለዋል።

130ኛው የዓድዋ ድል በዓል ''ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ'' በሚል ሀሳብ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም