የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም የተገኘ የአንድነት ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም የተገኘ የአንድነት ውጤት ነው
ሀዋሳ ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊነትን በማስቀደም የተገኘ የአንድነት ውጤት በመሆኑ ወጣቱ ትውልድ በልማት ሊደግመው ይገባል ሲሉ የታሪክ መምህራን ገለጹ።
የዓድዋ ድል ትውልዱ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ ለሚያደርገው ጥረት የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና መሰረት ይጥላል
የዓድዋ ድልን በማስመልከት ኢዜአ በሃዋሰ ከተማ ያነጋገራቸው የታሪክ መምህራን እንዳሉት፤ ወጣቱ ትውልድ የሀገሩን ታሪክ ጠንቅቆ በማወቅ የዓድዋ ድል እሴቶችን ማስቀጠል አለበት።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የታሪክ መምህርና ጋዜጠኛ ሰርክአለም አለማየሁ እንዳሉት፤ ወጣቱ ትውልድ ስለኢትዮጵያ ጠንቅቆ ማወቅ አለበት።
ኢትዮጵያውያን ሀገርን በማስቀደምና ሉአላዊነቷን ለማስከበር ዛሬ ድረስ ለመላው ጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነውን ደማቅ ታሪክ መስራታቸውን ተናግረዋል።
የአሁኑ ትውልድም በተለያየ አጋጣሚ ሀገርን የሚያሳንሱና ልማትን የሚያደናቅፉ አስተሳሰቦችን ወደጎን በማለት ሀገሩን በልማት ወደፊት ለማምጣት በአብሮነት መቆም አለበት ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ለሀገር ክብርና ሉአላዊነት በጋራና በአንድነት በመቆም የህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል የዓድዋን ድል አስመዝግበዋል ሲሉም ገልጸዋል።
የአሁኑ ትውልድም ከጀግኖች አባቶችና እናቶች ታሪክ ተምሮ የሀገርን እድገት አጠናክረው በሚያስቀጥሉ የልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ የራሱን ታሪክ መጻፍ እንዳለበት ነው የገለጹት።
የዓድዋ ድል ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ለወረራ የመጣውን የጣልያን ጦር ድል በመንሳት ዛሬ ድረስ በነጻነት ለመኖር መሰረት የጣሉበት የጀግንነት ታሪካችን ነው ያሉት ደግሞ የታሪክ መምህርና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዘርፍ ባለሙያ አቶ ዘለቀ ከበደ ናቸው።
በዓድዋ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ሉአላዊነት በጋራ በመቆም፣ ህብረታቸውን በማጠናከርና በመተጋገዝ ደማቅ ታሪክ መጻፋቸውን አስታውሰው፣ ይህን የሀገር ፍቅርና የአብሮነት ውጤት ወጣቱም ማስቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።
በተለይ የአሁኑ ትውልድ ከጀግኖች አባቶች ታሪክ በመነሳት ለሀገር ክብርና ልማት በአንድ ላይ በመቆም የራሱን አሻራ ማኖር እንዳለበት ነው የመከሩት።