ቀጥታ፡

የፕላስቲክ ከረጢት ክልከላን ለማሳካት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ህብረተሰቡ የፕላስቲክ ከረጢቶች ላይ የተጣለውን ክልከላ ተግባራዊ ለማድረግ እያበረከተ ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ። 

ባለስልጣኑ ከአምራቾች ጋር በመሆን ተኪ ምርቶች በስፋት ለተጠቃሚ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀዋሳ በፕላስቲክ ከረጢት ምትክ አማራጭ ምርቶችን የመጠቀም ልምድ እየዳበረ ነው

የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ እና አወጋገድ አዋጅ 1383/2017 ከጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ ሃገር ማስገባት፣ መሸጥና መጠቀም ላይ ሙሉ ክልከላ ማድረጉ ይታወቃል።

የኢፌዴሪ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ አዋጁ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር፣ የከተሞች መስፋፋት እንዲሁም የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ስርዓት መዘርጋትን መነሻ በማድረግ የተዘጋጀ ነው።


 

በለውጡ ዓመታት የተሰሩ የኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ፅዳት ማዕከል ያደረጉ እንዲሆኑ በማስቻል ንፁህና ፅዱ ለማድረግ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ አዋጅ ማዘጋጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

አዋጁ ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች(በተለምዶ ፌስታል የሚባሉት) ላይ ሙሉ በሙሉ ክልከላ ያደረገ አዋጅ መሆኑን አንስተዋል።

አዋጁ የበርካታ ሀገራት ልምድን ከመቀመር ባለፈ የፕላስቲክ ከረጢቶች በጤና ላይ የሚያደርሱትን አሉታዊ ተፅዕኖ ታሳቢ በማድረግ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።    

እነዚህ ፕላስቲክ ከረጢቶች ለካንሰር፣ ለአዕምሮ እድገት ውስንነት እና ለመተንፈሻ አካላት ህመሞች  ምክንያት መሆናቸውን አንስተው፤ የአፈር ለምነትን፣ ውሃ አየር እና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ እንደሆነ እንዲሁም የምግብ ዋስትናንና ሉዓላዊነትንም እንደሚያደናቅፍ አመልክተዋል።

የፕላስቲክ ከረጢት አጠቃቀም ልምድን ለመቀየር ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲክ ከረጢቶች ሙሉ በሙሉ መከልከላቸውን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአብዛኞቹ የሀገሪቷ አካባቢዎች ሕጉ ተፈፃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥብቅ የክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የአዋጁ ትግበራ የጊዜ ገደብ ተራዝሟል የሚል ሃሰተኛ መረጃ እየተሰራጨ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ በዚህ የተሳሳተ መረጃ ሳይዘናጋ ለአዋጁ ተፈፃሚነት የበኩሉን ሚና መወጣቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

ባለስልጣኑ ከአምራቾች ጋር በመሆን አማራጭ ምርቶች በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ በዚህም አብዛኛው ኢንዱስትሪዎች ምርቶችን በስፋት እያመረቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አሁንም ምርትን በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ መስራት እንደሚጠይቅ ጨምረው አስታውቀዋል።

በአካባቢ ላይ የሚደርሱ ብክለቶች ዙሪያ ጥቆማ የሚያደርሱበት እንዲሁም ቅሬታ የሚያቀርቡበት የዲጂታል ስርዓት ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር እየተዘረጋ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም