በሀዋሳ በፕላስቲክ ከረጢት ምትክ አማራጭ ምርቶችን የመጠቀም ልምድ እየዳበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ በፕላስቲክ ከረጢት ምትክ አማራጭ ምርቶችን የመጠቀም ልምድ እየዳበረ ነው
ሀዋሳ ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በሀዋሳ ከተማ በፕላስቲክ ከረጢት ምትክ አማራጭ ምርቶችን የመጠቀም ልምድ እየዳበረ መምጣቱን የከተማ አስተዳደሩ አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡
በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 1383/2017 መሠረት እንደ ሀገር ከጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት፣ ወደ ሀገር ማስገባት፣ መሸጥና መጠቀም ላይ ክልከላ ተደርጓል፡፡
አዲስ አበባ በንፅህና አጠባበቅ ረገድ እያከናወነች ያለው ሥራ በአርዓያነት ይጠቀሳል
ባልተገባ መልኩ የሚጣሉ የፕላስቲክ ከረጢቶች /ፌስታል/ አካባቢን በመበከል፣ የውሃ መስመሮችን በመዝጋት፣ በተለይ ሳይበሰብሱ ለብዙ ዓመታት በመቆየት የስነ ምህዳር ጠንቅ እንደሆኑ ሳይንሳዊ ምርምሮች ያወሳሉ።
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ከረጢት አጠቃቀምን ለመገደብና ለመከልከል ባለፉት ዓመታት በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን ክልከላው በዋናነት የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስና የህዝብን ጤና ለመጠበቅ ያለመ መሆኑም ይታወቃል።
ይህንን ተከትሎ በሀዋሳ ከተማም ክልከላው ተግባራዊ እየተደረገ ሲሆን በህብረተሰቡ ዘንድ በፕላስቲክ ከረጢት ምትክ አማራጭ ምርቶች የመጠቀም ልምድ እየዳበረ መምጣቱን የጽህፈቱ ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሹምባሻ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
ጽህፈት ቤቱም ክልከላውን ከማስተግበር ጎን ለጎን ምትክ ምርቶች በስፋት ለሕብረተሰቡ እንዲቀርቡ እየሰራ እንደሚገኝ ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ወቅት በከተማዋ 15 ድርጅቶች ምትክ የወረቀት ከረጢቶችን በማምረት ሥራ ላይ በመሰማራታቸው አዋጁን ከመተግበር ባለፈ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል ብለዋል።
የኤሊያና ፔፐር ፓኬጂንግ ኤንድ ማኑፋክቸሪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ ሞገስ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው የወረቀት ከረጢቶችን በስፋት የማምረት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ ስነ ምሕዳሩን ከመጠበቅ ባለፈ በዘርፉ ተጨማሪ የገበያ ዕድል በማስገኘት ሰፊ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅትም 85 ወጣቶችን በማሰልጠን የስራ እድል ለመፍጠር የተቻለ ሲሆን በቀን እስከ 15 ሺህ የወረቀት ከረጢቶችን እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሱፐር ማርኬት ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ፀሐይ ይርዳው በበኩላቸው፤ የጨርቅ ከረጢቶችና ካርቶኖችን በመጠቀም ደንበኞቻቸውን እያስተናገዱ እንደሚገኙ ይገልፃሉ።
ከዚሁ በተጨማሪም ማህበረሰቡ አምኖበት የወረቅ ምርቶቹን እንዲጠቀም ለማድረግም ግንዛቤ የመፍጠር ስራ እየሰሩ መሆኑን ነው ያነሱት።
በሆቴል ሥራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ ልደት ማሩፋ፤ የፕላስቲክ ከረጢት ክልከላው ሀዋሳን ፅዱ ከማድረግ ባለፈ ሀይቁን ከብክለት ሥጋት ነፃ የሚያደርግ በመሆኑ በደስታ እንደተቀበሉት ገልፀዋል፡፡
ለቤታቸው በሚሸምቱት ዕቃም ሆነ በሆቴል አገልግሎታቸው አማራጭ ምርቶችን ብቻ እየተጠቀሙ መሆኑን ተናግረው የክልከላ አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆንና ፅዱ ከተማን ለመፍጠር ሁሉም መተባበር እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡