ቀጥታ፡

የብልጽግና ፓርቲ የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ባደረጋቸው ጥረቶች የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ ያስቀጥላል

ወልቂጤ ፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ)፡- የብልፅግና ፓርቲ  ያሉትን ፀጋዎች ወደ ውጤት በመቀየር የህዝብን የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ባደረጋቸው ጥረቶች የተገኙ  ስኬቶችን አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተገለፀ።

የብልፅግና ፓርቲ በጉራጌ ዞን  ''ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር'' በሚል መሪ ሃሳብ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመወዳደሪያ ምልክት (የስንዴ ነዶ) እና የማኒፌስቶ የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል። 

በወቅቱም የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት፣ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ባደረጋቸው ጥረቶች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል።


 

በተለይም በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎች ወደ ውጤት እንዲቀየሩ በተደረጉ ጥረቶች ውጤቶች መመዝገባቸውን አውስተው ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ በእርሻና በእንስሳት ልማት የተገኘውን ውጤት አንስተዋል።

ዞኑ ያለውን አቅም ለመጠቀም በተደረገው ጥረት በእርሻ ኢንዱስትሪ በመሰረተ ልማትና በሌሎችም የልማት ስራዎች የዜጎችን ህይወት ያሻሻሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰው ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ፓርቲው አበክሮ ይሰራል ብለዋል።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስርዓትን በመዘርጋት በስንዴ ልማትና በምግብ ራስን ለመቻል በተሰሩ ስራዎች እንዲሁም ውብና ፅዱ አካባቢን በመፍጠር ረገድ የሃገራችን ስም በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እየተወሳ መሆኑን  ጠቅሰዋል።

ፓርቲው እነዚህን የልማት ስኬቶች ለማስቀጠል ይተጋል ያሉት አቶ ላጫ አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባትና ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ህዝቡን የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የተመዘገቡ የልማት ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል እንደ ሀገር የተወጠነውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ  በትጋት ይሰራል ብለዋል።

በጉራጌ ዞን ያለውን ፀጋ በመጠቀም አርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በማድረግ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና የስራ እድል ለመፍጠር ያስቻሉ ውጤቶች መገኘታቸውን ያነሱት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የጉራጌ ዞን ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ገብረመስቀል ናቸው።


 

ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተደረገው ርብርብ ፍሬ እያፈራ መሆኑን በመጠቆም የህዝቡ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን አንስተዋል።

ፓርቲው  ሰው ተኮር ለሆኑ የልማት ስራዎች በሰጠው ልዩ ትኩረት የዜጎችን ህይወት የቀየሩ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተው በየጊዜው በዞኑ  የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በዘላቂነት ለመፍታት እንደሚሰራም ተናግረዋል። 

በመድረኩም የዞንና የከተማ አስተዳደሮች የስራ ሃላፊዎች፣  የወጣትና ሴቶች አደረጃጀቶች እና ደጋፊዎች ተገኝተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም