ቀጥታ፡

ምርጫው ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት እንዲሆን እየሰራን ነው- ፓርቲዎች

ደሴ ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት እንዲሆን እየሰራን ነው ሲሉ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክሮች ለሀገርና ህዝብ በሚጠቅሙ የፖሊሲ አጀንዳዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል

በአማራ ክልል ደሴ ከተማና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት በደሴ ከተማ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።


 

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢና በኢዜማ የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ሻምበል ደምሌ ተረፈ፤ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት መዳበርና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ምርጫ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ የጋራ ምክር ቤቱ የዘንድሮው ምርጫ በሃሳብ የበላይነት በመፎካከር ሀገርን አሸናፊ የሚያደርግ እንዲሆን ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት እንዲሆን እየሰራን ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የዛሬው ውይይት ዋነኛ ዓላማም በምርጫው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጋራ በመፍታት ሰላማዊ፣ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢና በብልጽግና ፓርቲ የደሴ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ፤ ለምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሂደት የጋራ ምክር ቤቱ አባላት በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።


 

ለምርጫው ተወዳዳሪ እጩዎችንና ታዛቢዎችን መመልመላቸውን ጠቁመው በቅስቀሳ ወቅት ከጠብ አጫሪነትና ጥላቻ ንግግሮች በመራቅ መራጩ የጠራ ግንዛቤ አግኝቶ እንዲወስን ማድረግ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የጋራ ምክር ቤቱ አባልና የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ የደሴ ቅርንጫፍ ተወካይ አቶ ያለው አሸብር፤ በሀገር ዘላቂ ሰላም፣ ጥቅምና ልማት ፓርቲያችን አይደራደርም ብለዋል።


 

በወሎ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ መሀመድ የሱፍ፤ በቅደመ ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ ምርጫ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል የዛሬው ምክክር ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።


 

በሁሉም ፓርቲዎች ዘንድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስተካከል የተሳካ ምርጫ ለማካሄድ የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም