ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክሮች ለሀገርና ህዝብ በሚጠቅሙ የፖሊሲ አጀንዳዎች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል- ምሁራን

ሮቤ፤ የካቲት 20/2018 (ኢዜአ)፡-የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክሮች ለሀገርና ህዝብ በሚጠቅሙ የፖሊሲ አጀንዳዎች ላይ ያተኮሩ መሆን እንዳለባቸው የመደ ወላቡ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውንና ስትራቴጂዎቻቸውን በመገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ ማስተዋወቅ ጀምረዋል። 

ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒ እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጎላ ሚና እንዳላቸው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገልጸዋል።

ፓርቲዎች በምረጡኝ ቅስቀሳቸው ከጥላቻ ንግግሮች መራቅና ሀሳባቸውን በሰለጠነ መንገድ መግለጽ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ያግዛል ነው ያሉት ምሁራኑ።

ፓርቲዎቹ የሚያቀርቧቸው አማራጭ ሀሳቦች ወደ መሬት ሊወርዱ የሚችሉና ሀገርን የሚያሻግሩ ሊሆኑ እንደሚገባም አንስተዋል።

በዩኒቨርስቲው የስነ ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት መምህርና ተመራማሪ መቅደስ መስፍን እንዳሉት፣ ጠቅላላ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅሰቀሳ ወቅት በከፍተኛ ኃላፊነት ሊሳተፉ ይገባል።

ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ለሀገር የሚበጅና ሊያሻግር የሚችል አማራጭ ፖሊሲና ስትራቴጂያቸውን በሰለጠነ መልኩ ሊያንጸባርቁ ይገባል ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተዓማኒነት እንዲሆን የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የምርጫ ሥነ-ምግባር ሕጉን ባከበረ መልኩ መንቀሳቀስ አለባቸው ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጋዜጠኝነትና ሥነ- ተግባቦት ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ኡመር መሐመድኑር ናቸው።

በአሁን ጊዜ ፓርቲዎቹ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አማራጮች አያደረጉት ያለው ክርክር በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሚኖረው በመከባበር ላይ የተመሰረተ ሲሆን ነው ብለዋል።

በዩኒቨርሲቲው የጂኦግራፊና አካባቢ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ተስፋዬ ፈዬ (ረዳት ፕሮፌሰር) በበኩላቸው የፓርቲዎች ንግግርም ሆነ ተግባር  ህዝብን ያከበረ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ የሚያነሱት አማራጭ ሀሳብ ሕብረተሰቡ በቀላሉ ሊረዳው በሚችለው አግባብ መቅረብ እንዳለበትም አንስተዋል።

በምርጫው ቅስቀሳና ክርክር ወቅት የሀገርን አንድነትና ሉአላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ንግግርም ሆነ ተግባር መፈጸም ተገቢ እንዳልሆነ በመረዳት ፓርቲዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ረዳት ፕሮፌሰሩ ያስገነዘቡት።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም