የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት ያስችላል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እንደሚያስችል የኢፌዲሪ የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ገለጸ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮችና በውጭ ዓለማት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
የሀገራዊ ምክክር ሂደቱን በስኬታማነት ለማስቀጠል የሁሉም አካላት ሚናና ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል
ዋናውን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለማካሄድም የአጀንዳ ቀረፃና የግብዓት ማሰባሰብ የዝግጅት ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል።
በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመኑ በ1ኛ ዓመት አስቸኳይ ጉባኤም የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመን ለሁለተኛ ጊዜ ለሚቀጥሉት ስምንት ወራት ተራዝሟል።
የኢፌዲሪ የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ኃይለየሱስ ታዬ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ብሔራዊ መግባባት ለጠንካራ ሀገረ መንግስት፣ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ለዚህም በሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም ዙሪያ የዜጎችን ግንዛቤ በማሻሻል የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ተግባራትም የዜጎችን ግንዛቤ በማሳደግ ሕብረብሔራዊ አንድነትን እያጎለበቱ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በቀጣይም በክልሎች ጭምር የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የዜጎችን የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም ሥርዓት ግንዛቤ ለማጎልበትም በተለያዩ የህዝብና የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መልዕክቶችና ትምህርቶች እየተላለፉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም መግባባት ባልተደረሰባቸው ዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር የጋራ መግባባትን ለመፍጠር መሠረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያውያንም በሀገራዊ ምክክሩ የተመቻቸውን ዕድል በመጠቀም ብሔራዊ መግባባትን መፍጠርና ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።
የሕገ-መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከልም ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት በዕውቀት ላይ የተመሰረቱ አጋዥ ሃሳቦችን በማፍለቅ እንደሚሰራ አንስተዋል።