ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ሆነዋል

ባህር ዳር ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለፀ።

ቢሮው የመማር ማስተማር ስራን የሚገመግም እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ይገኛል።


 

የቢሮ ኃላፊው አቶ ጥላሁን ወርቅነህ በመድረኩ እንዳስታወቁት፤ የመማር ማስተማር ስራውን በተሳትፎም ሆነ ጥራትን ለማረጋገጥ በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት እየተመዘገበ ነው።

በአማራ ክልል የማህበራዊ ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ነው

ከትምህርት ማህበረሰቡ ጋር በተደረገ የቅንጅት ስራ በጸጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት አቋርጠው ከቆዩ ተማሪዎች በርካቶቹን ወደ ትምህርት ገበታ መመለስ እንደተቻለ ገልፀዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ ደረጃቸውን የጠበቁ ተቋማትን የመገንባትና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላት ተግባር በትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በዚህም ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የአራት ሞዴል ሁለተኛ ደረጃና የሦስት አዳሪ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ሲሆን በ2019 የትምህርት ዘመን ስራ ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

በክልሉ መንግስትና በአጋር አካላት ትብብር በተመደበ አንድ ቢሊዮን ብር በጀት ከ600 ሺህ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አስረድተዋል።

የምገባ ፕሮግራሙም ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እና የማቋረጥ መጠንንም በመቀነስ ረገድ የጎላ ሚናን እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።

ዘግይተው ወደ ትምህርት ቤት የመጡ ተማሪዎችን ለማብቃት በተፋጠነ የትምህርት አቀራረብና ማካካሻ የመማር ማስተማር ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።


 

በባህር ዳር ከተማና ዙሪያዋ በሚገኙ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ከ150 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ ሙሉአለም አቤ (ዶ/ር) ናቸው።

በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በተያዘው የትምህርት ዘመን ከ286 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የአስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታው አለሙ ናቸው።


 

ለሁለት ቀን በሚቆየው መድረክም የክልልና የዞን የዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን ያለፉት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም