ቀጥታ፡

ከዛፍ የሚታለብ ወተት

በቀደሰ ተክሌ -(ከሚዛን አማን ቅርንጫፍ)

ጥበብ ከተፈጥሮ ጋር ስትገናኝ ሌላ እውነት ሌላ አዲስ ነገር ትፈጥራለች። የሰው ልጅ የመመራመርና የማወቅ ተፈጥሯዊ ባህርይው በተፈጥሮ ላይ ሁሉን የማድረግ ሥልጣንን ያስቸረ ነው። ሰው ያልነበረን አዲስ ነገር መፍጠር ባይችልም፤ ከነበረው ሌላ ውጤት ማግኘት ወይም መፍጠር ይችላል።

"ጉማታ" በረከትን የመጋራት እሴት!!

በዓለማችን ሰውን እና እቃን ከቦታ ወደ ቦታ የማንቀሳቀስ ትልቅ አገልግሎት ያለው ተሽከርካሪ ሕይወት ያለው መስሎ እንዲታይ የሚያደርገው የተገጠመለት ጎማ ነው።

ታዲያ ይህ ጎማ ከዛፍ በተገኘ የወተት ጠብታ የሚሰራ መሆኑ አግራሞትን ከሚፈጥሩ የጥበብ ሥራ ውጤቶች መካከል እንዲሆን ያደርገዋል። የጎማ መስሪያ የሆነው ጥሬ ምርት ከዛፍ እንዴት እንደሚዘጋጅ ከስፍራው ኢዜአ የተመለከተውን ሊያስቃኛችሁ እነሆ ይላል፡-

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጎማ ዛፍ ልማት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቤንች ሸኮ ዞን ጉራ ፈርዳ ወረዳ  ይገኛል።

በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛ የተባለው ይህ የጎማ ዛፍ ልማት በ3 ሺህ 884 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው።

አረንጓዴ ካባ የደረበውን የበበቃ ቀዬ እንደተሻገሩ ቀጥ ቀጥ ብለው የቆሙ  ዛፎች ቅርንጫፋቸውን ከመሬት ከፍ አድርገው ግንዱን ለሌላ ተግባር እየተዉ አድገው በአዲስ ብርሃን ቀበሌ ደምቀው ይታያሉ።


 

እነዚህ ዛፎች ከወገብ በታች ባለው ክፍል ብዙ ሺህ ጅራፍ እንዳረፈበት ገላ ሰምበር በሰንበር ሆነዋል። ይህም ሌሊት ሌሊት በሚፈጸም ከዛፉ ወተት ለማምረት በተደረገ ጥረት ሳቢያ የተፈጠረ ነው። 

ጎማን ለመሥራት የሚያስችለውና ከዛፉ የሚገኘውን ወተት ማምረትም የሰለጠኑ ባለሙያዎች ሌሊት ከ9 ሰዓት ጀምሮ የሚከውኑት ተግባር ነው።

ይህን ሥራ ለማቀላጠፍም ከ500 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች ላይና ታች ይላሉ። ሠራተኞቹም ራሳቸውን ከማስተዳደር ባለፈ በወዝ በላባቸው ለሀገር አዎንታዊ ተጠቃሚነት የሚውለውን ምርት ያቀርባሉ።

የጎማ ዛፍ በተፈጥሮ ብዙ ወተት የሚይዘው ሌሊት ነው። ቀን የሰበሰበውን ወተት ሌሊት ያለ ስስት ይለግሳል። በዚህን ሰዓት ዛፉን አድምተው ወተት ሊያልቡ የተዘጋጁ ሠራተኞች በሰለጠኑት ሙያ መሠረት የፀሐይ መውጫና መግቢያ አቅጣጫን ቀድመው ይለያሉ።

የፀሐዩን አቅጣጫ ከለዩ በኋላ በዛፉ ሰሜንና ደቡብ አቅጣጫ ጎን ላይ በስለታማ ቁስ በአንድ መስመር ቀጥ አድርገው በመፈቅፈቅ ለዛፉ ወተት መውረጃ ቦይ ያበጃሉ። በመቀጠል ሁለቱን መስመሮች ከፊት ለፊት የሚያገናኝ ሌላ መስመር በማበጀት የዛፉ ወተት መሰል ፈሳሽ ከስር ወደተቀመጠው ፈሳሽ መቀበያ ባልዲ ያለ ስስት ይፈሳል። 


 

የጎማ ዛፍ ወተት ጠብታ ከእያንዳንዱ ዛፍ ስር ተሰብስቦ በብዙ ሊትር ተመዝኖ በበርሜል ይከማቻል። በአግባቡ የማጣራትና አሲድ ጨምሮ የማርጋት ሥራ ወደ ሚሰራበት ክፍል ይገባል። ወተቱ ከረጋ በኋላም ይታጠባል። ተድጦ የሚፈለገውን ያህል ቅርጽ ከያዘ በኋላ ጋቢ መስሎ ፀሐይ ላይ ይሰጣል። 


 

በፀሐይ ኃይል ጠፈፍ እንዲል የተሰጣው ምርት የተያዘለት ሰዓት ሲጠናቀቅ በባህላዊ መንገድ ወደ ተዘጋጀው ጭስ ቤት ይላካል።  በዚህ ክፍል ውስጥ ለዚሁ ተግባር የሚያገለግሉ በተለያየ ደረጃ የተዘጋጁ እሳት ማንደጃ ጉድጓዶች ይገኛሉ። ከፀሐይ ላይ ተሰጥቶ ወደ ውስጥ እንዲገባ የተደረገው ምርት በዚህ ክፍል ከ5 እስከ 6 ቀናት የተለያዩ የድርቀት ደረጃዎችን እየተሸጋገረ ይቆያል። በጥሩ ሁኔታ ቀይ ሆኖ ከደረቀ በኋላ ለጎማ ኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ሆኖ ለሽያጭ ዝግጁ ይሆናል።


 

ሁለት አስርተ ዓመታትን ያስቆጠረው የጎማ ልማትና ምርት ሥራ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን የጎማ ጥሬ ዕቃ በከፊል በመሸፈን በሀገራዊ ኢኮኖሚው ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል። 

በኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የጎማ ዛፍ ልማትና ምርት ፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘማች ሳድንስ እንደሚሉት፤ የጎማ ዛፍ አንድ ጊዜ ከተተከለ በኋላ ዓመቱን ሙሉ ምርት የሚሰጥ ዛፍ ነው። የወተት ምርት ለመስጠት ችግኙ ከተተከለ በኋላ ለሦስት ዓመታት ይቆያል። 


 

በጉራፈርዳ ወረዳ ለምቶ ምርት እየሰጠ ካለው ዛፍ  በወር  ከ37 እስከ 40 ቶን የጎማ ዛፍ ጥሬ ምርት በመመረት ላይ ሲሆን ዘንድሮ ከ560 ቶን በላይ ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የዘርፉን የጥሬ ምርት ፍላጎት በከፊል ለመመለስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከ87 ሺህ ሄክታር በላይ ለጎማ ዛፍ ምቹ መሬት እንዳላት ጥናቶች ያመለክታሉ። ይሁን እንጂ በስፋት ወደዚህ ዘርፍ በመግባት የዘርፉን ኢኮኖሚ መጠቀም አልተቻለም። የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን የጎማ ዛፍ ልማትን ለማስፋፋት አቅዶ በጥናት ከተለዩ ቦታዎች መካከል በኦሮሚያ ክልል ኢሉአባቡር ዞን ከ2 ሺህ 500 ሔክታር በላይ መሬት ተረክቦ ችግኝ የማዘጋጀት ተግባር እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም የሀገር ውስጥ የጥሬ ምርት ፍላጎትን በሀገር ውስጥ በመሸፈን እና የተረፈውን ኤክስፖርት በማድረግ ከዘርፉ የውጭ ምንዛሬ ማግኘት የሚቻልበትን ዕድል ለመፍጠር ትኩረት መደረጉን አቶ ዘማች ጠቁመዋል። ባለሃብቶች ወደዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ ሀገርን የሚጠቅሙ ውጤቶችን ማምጣት እንደሚቻልም አክለዋል።

ኢትዮጵያ በየዘርፉ ያላት የኢኮኖሚ አቅም የዕድገት ጉዞዋ አቅሞች ናቸው። በተለይ ለም አፈሯ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ምርቶችን በማብቀል ለሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሀብት መፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን በብዙ መንገድ ማረጋገጥ እየተቻለ ነው። ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው የጎማ ዛፍ ልማትም ከእነዚህ አቅሞች አንዱ ነው።

ያሉንን ጸጋዎች ለይቶ ለማልማትና ምርታማነትን ለመጨመር መንግሥት የሰጠውን ትኩረት መሠረት በማድረግ የጎማ ዛፍ ምቹ አጋጣሚዎችን ለይቶ መሥራት ከተቻለ ከዘርፉ በብዙ መጠቀም ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም