ቀጥታ፡

"ጉማታ" በረከትን የመጋራት እሴት!!

"ጉማታ" በረከትን የመጋራት እሴት!!

በያንተስራ ወጋየሁ -ዲላ 

ቀን ቀንን እየወለደ ጊዜ ሳያቋርጥ እንደ ዥረት መፍሰሱን አያቆምም። ትናንት አዲስ የነበረው አሮጌው የሚባልበት፣ ዛሬ አዲስ ሆኖ ነገ አሮጌ ለመባል ይሮጣል።

ወቅቶች ይፈራረቃሉ፣ ይመሻል፣ ይነጋል፣ ትናንት ለዛሬ፣ ዛሬ ለነገ እንዲህ እንዲህ እየተቀባበሉ ዘመን ዘመንን እየተካ ዛሬ ላይ ተደርሷል።


 

በጥምር ግብርናውና በቡናው የሚታወቀው ጌዴኦ ትናንትን ሸኝቶ ዛሬን እንደ አዲስ ለመቀበል ሽር ጉድ እያለ ነው።

በክረምቱ የተዘራው ሰብል ተሰብስቦ ወደ ጎተራ እንዳስገባ ጌዴኦ አዲስ ዓመቱን ‹‹ዳራሮ››ን ይቀበላል።

ዳራሮ የተጣላ የሚታረቅበት፣ ቂም የያዘ ቂምና ቁርሾውን የሚተውበት፣ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ አዛውንቶች ወደ ሽምግልና የሚሸጋገሩበት እሴቶችን በውስጡ የያዘ ነው።


 

"ያገኘሁትን ምርት ብቻዬን አልበላም" ብሎ የሚያምነው የጌዴኦ አርሶ አደር ካመረተው ምርት ለመሪው፣  ልጆች ለወላጆችና ለአሳዳጊዎቻቸው፣ አዲስ ተጋቢዎች ለአማቾቻቸው፣ ቂም የያዘ ሰው እንዲሁ የተቀየመውን ሰው ይቅርታ ለመጠየቅ ጉማታ ይዘው ይሄዳሉ።

"ጉማታ" በጌዴኦ ዘመን መለወጫ ወቅት የሚፈጸም ስጦታ ነው።

ጉማታ በቤት ውስጥ ተዘጋጅቶ ወደ ታላላቆች ቤት ወይም ወደ ማኅበረሰቡ አደባባይ የሚወሰድ በመሆኑ፣ የግለሰብን ደስታ ወደ ማህበረሰባዊ ደስታ የሚቀይር ድልድይ ነው።

በአጠቃላይ ጉማታ ከሌለ የዳራሮ በዓል ሙሉ አይሆንም። ጉማታ የጌዴኦን ሕዝብ አንድነት የሚያጸና፣ ትውልድን ከትውልድ የሚያስተሳስር ሀገር በቀል እሴት ነው።

በዳራሮ በዓል አከባበር ውስጥ "ጉማታ" እጅግ አስፈላጊና ትልቅ ትርጉም ያለው ባህላዊ የክብር ስጦታ የመስጠት ሥርዓት ነው። 

"ጉማታ" ማለት በቀጥታ ትርጉሙ "ስጦታ" ማለት ቢሆንም፣ በጌዴኦ ባህል ግን ከስጦታ በላይ ነው። ምስጋናን፣ ፍቅርን፣ አክብሮትንና በረከትን የመጋራት መገለጫ ነው።


 

የጌዴአ ባህላዊ የባሌ ስርዓት መሪ ሆነው የሚሰየሙት አባ ገዳ ለህዝብ ከመጸለይ፣ ከማስታረቅና ክፉን በማውገዝ ህዝቡ ተፈጥሮን እንዲንከባከብ ከማስተማር ውጭ አይዘሩም፣ አይነግዱም፣ አልፎም እንሳስትን አያረቡም፡፡ የዳራሮ በዓልን ተከትሎ ህዝቡ የሚያቀርብላቸውን "ጉማታ" በመቀበል ባህላዊ የመሪነት ሚናቸውን በአግባቡ ከመወጣት ውጪ። 

ኑሮው ከጥምር እርሻ ጋር የተቆራኘው የጌዴኦ ሕዝብ ዘርቶ ካጨደው፣ አርብቶ ካገኘው ከብት፣ አንቦ ከቆረጠው ማር፣ ከሁሉም በአይነት በአይነቱ ሸክፎ ዳራሮ ወደ ሚከበርበት ሶንጎ (አደባባይ) ይተማል።

ለጉማታ ከሚቀርቡ ከፍተኛ ዋጋ ያላቸው ስጦታዎች አንዱ ማር ነው። ማር በጌዴኦ ዘንድ የጣፋጭ ዘመንና የጤና ምልክት ተደርጎ ይወሰዳልና ዋናው ስጦታ ነው።

ጌዶኦዎች ቡና፣ ቅቤና ባህላዊ ምግቦች፣ የቁም እንስሳት በግና ስንጋ እንዲሁም ገንዘብ በመያዝ በበዓሉ ውስጥ የጉማታ ስርዓት ሲደርስ ተሽቀዳድመው ለአባ ገዳው በመስጠት ምርቃት ይቀበላሉ።


 

"ጉማታ" የተቀበለው ሰው የሚመርቀው ምርቃት በሰጪው ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ ይታመናልና ከስጦታው ይልቅ ምርቃቱ ትልቅ ዋጋ አለው። 

"ያገኘሁትን ምርት ብቻዬን አልበላም" ብሎ የሚያምነው ጌዴኦ በረከትን ማካፈል ለቀጣዩ ዓመት ተጨማሪ በረከት እንደሚያገኝ ስለሚያውቅ ጉማታ መስጠት የዘመናት ቅርሱ ነው።

ጉማታ ከአባ ገዳና ከባህል ሽማግሌዎች ባለፈ አርሶ አደሩ ከማጋኖ (ከፈጣሪ) ያገኘውን በረከት ለሚወዳቸውና ለሚያከብራቸው ሰዎች የሚያቀርብበት መንገድ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ  ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።


 

ልጆች ለወላጆቻቸውና ለቤተሰብ አባላት ላሳደጓቸውና ለሰጧቸው ምርቃት ምስጋናቸውን ለመግለጽ ጉማታ ይዘው ይሄዳሉ። በቅርቡ ጋብቻ የመሠረቱ ወጣቶች ወደ አማቾቻቸው ቤት ጉማታ ይዞ በመሄድ ዝምድናቸውን ያጠናክራሉ።

በዓመቱ ውስጥ ቅሬታ ወይም ቂም ካለ፣ በዳራሮ ወቅት ጉማታ ይዞ በመሄድ ይቅርታ ይጠየቃል። ጉማታ የሰውን ልብ ለማለስለስና አዲስ ዓመትን በሰላም ለመጀመር ያገለግላል ተብሎ ስለሚታመን።

ጉማታ በቤት ውስጥ ተዘጋጅቶ ወደ ታላላቆች ቤት ወይም ወደ ማህበረሰቡ አደባባይ የሚወሰድ በመሆኑ፣ የግለሰብን ደስታ ወደ ማህበረሰባዊ ደስታ የሚቀይር ድልድይ ስለመሆኑም ነው ዋና አስተዳዳሪው የጠቆሙት።

በአጠቃላይ ጉማታ ከሌለ የዳራሮ በዓል ሙሉ አይሆንም። ጉማታ የጌዴኦን ሕዝብ አንድነት የሚያጸና፣ ትውልድን ከትውልድ የሚያስተሳስር ሀገር በቀል እሴት ነው።

ይህም የመደጋገፍ እሴትን ከማጠናከር በተጓዳኝ ህዝቡ የመንግስት ገቢን እንዲሁም በማህበረሰብ ተሳትፎ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን መሰረት የጣለ ነው ይላሉ። 


 

የዘንድሮው ዳራሮ ከቤት በተለይም ከአባ ገዳው መኖሪያ አንስቶ በሶንጎዎችና በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ጭምር እየተከበረ መሆኑን ያነሱት አስተዳዳሪው ጉማታም ዋናው የበዓሉ እሴት ሆኖ እየተከበረ ነው ብለዋል።

ባህልና ማንነትን በማስጠበቅና በማዳበር፣ ባህሉ ወደ ወጣቶች እንዲተላለፍ በማበረታታት እንዲሁም የጌዴኦ ባህልን ለሌሎች ህዝቦች ለማስተዋወቅና የማህበረሰብ አንድነትና ባህላዊ እሴትን ለማጠናከር እያገለገለ ያለው የጌዴኦ ዘመን መለወጫ ዳራሮ ጥር 29 እና 30 በዲላ ከተማ ይከበራል።

የዳራሮ በዓል የጌዴኦን ሕዝብ የሥራ ባህል፣ የተፈጥሮ ጥበቃ ዕውቀትና የሰላም እሴት ለዓለም የሚያሳይ ትልቅ አጋጣሚ ነው።

ይህ በዓል በተለይ የጌዴኦ የባህላዊ መልክዓ ምድር (Cultural Landscape) በዩኔስኮ (UNESCO) በዓለም ቅርስነት መመዝገቡን ተከትሎ፣ አሁን ላይ ከቤትና ከአደባባይ አልፎ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት እያገኘ ያለ ታላቅ እሴት ሆኗል።

የዓመት ሰው ይበለን!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም