የዓድዋ ድል ትውልዱ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ ለሚያደርገው ጥረት የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና መሰረት ይጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል ትውልዱ የሀገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ ለሚያደርገው ጥረት የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና መሰረት ይጥላል
ደሴ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ የዓድዋ ድል በደምና በአጥንት የተጻፈ የትናንት ታሪክ ብቻ ሳይሆን የዛሬው ትውልድ ሀገርን ለማበልጸግ የሚጠቀምበት የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና መሠረት መሆኑን በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን ገለጹ።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚሰሩ ምሁራን የአሁኑ ትውልድ አባቶቹ በአጥንትና በደም ያቆዩትን ሀገር የዘመኑን ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በመታጠቅ ድህነትን በማሸነፍ ሊደግመው ይገባል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ጋሻው መሐመድ(ዶ/ር) የዓድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ፣ የይቻላል ሥነ-ልቦና የፈጠረ ታሪካዊ ክስተት ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ድል ትምህርት መውሰድ እንዳለበት ጠቅሰው፣ በልማት ሥራዎች በንቃት በመሳተፍ፣ የሀገርን አንድነት በጽኑ መጠበቅና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የራሱን ታሪክ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ፈጣን ዕድገት ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ ብልጽግና መሰረት እየጣለና የዓለምን ትኩረት እየሳበ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ጉዞ ተጠናክሮ ሊቀጥል የገባል ብለዋል።
ሌላው በዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ አሰፋ ባልቻ(ዶ/ር) የዓድዋ ድል ዋነኛ ሚስጥር አንድነት መሆኑን ገልጸዋል።
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን ወራሪ ኃይል ድል ያደረገው የኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድና አልበገር ባይነት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ወጣቱ የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ አውቆና አክብሮ ዘመናዊ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በመታጠቅ የራሱን ታሪክ መስራትና የሀገርን ህልውና ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የዓድዋ ድል ትላንት በጦር ሜዳ የተመዘገበ የጀግንነት ታሪክ ብቻ ሳይሆን ዛሬ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ ለሚደረገው ጥረት የአሸናፊነት ሥነ-ልቦና መሰረት የሚጥል መሆኑንም ነው የገለጹት።
130ኛው የዓድዋ ድል በዓል ''ከአኩሪ ታሪክ ወደ ብሩህ አድማስ'' በሚል ሀሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።