ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የሰላም ስኬት ቁልፍ ሕዝቡን የሰላም ባለቤትና ተሳታፊ ማድረጋችን ነው - ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ያለው አስተማማኝ ሰላም ዋነኛ ምንጩ ሕዝቡን የሰላም ባለቤትና ዋና ተሳታፊ ማድረግ መቻሉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

8ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና ፀጥታ የጋራ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ሕዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለልማት ስራዎች መፋጠን ምቹ መደላድል ፈጥረዋል

የሰላም ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በጋራ ያዘጋጁት ይህ የምክክር መድረክ "ሰላማዊ ፖለቲካ ለሀገራዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሄደ ያለው።


 

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሰላም የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዋነኛና መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል።  

በመዲናዋ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሕዝብን የሰላም ባለቤት የሚያደርጉ ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል። 

ነገን የተሻለ ለማድረግ ዛሬ መስራት ይገባል ያሉት ከንቲባዋ ለዚህም አስተማማኝ ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።  

ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሕዝብን እሴት ማሳደግና መልካም ማህበራዊ መስተጋብርን ማጎልበት እንደሚገባም አፅንኦት ሰጥተዋል። 

አዲስ አበባ በዚህ ረገድ በምሳሌነት የምትጠቀስባቸው በርካታ ስራዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።

ለአብነትም በመዲናዋ የተመዘገበው አስተማማኝ ሰላም ዋነኛ ምንጩ ሕዝቡን የሰላም ባለቤትና ዋና ተሳታፊ ማድረግ መቻሉ መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ ሁለቱንም በማረጋገጥ የሕዝብን ተጠቃሚነት ማሳደግ የመንግስት ትኩረት መሆኑን ገልጸዋል። 

በአዲስ አበባ ያለውን አስተማማኝ ሰላም ዘላቂነት በማረጋገጥ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።

የምክክር መድረኩ ሰላምን ዘላቂ ማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በስፋት ለመወያየት ምቹ አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል።

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት እንዲከናወን ከወዲሁ የተቀናጀ ሥራ መሥራት እንደሚገባም ነው ከንቲባዋ የጠቆሙት።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር መሐመድ እድሪስ፣ የክልል ምክትል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የሰላምና ፀጥታ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም