ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ ሕዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለልማት ስራዎች መፋጠን ምቹ መደላድል ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2018(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብን የሰላም ባለቤት በማድረግ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ለልማት ስራዎች መፋጠን ምቹ መደላድል መፍጠራቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።

8ኛው ሀገር አቀፍ የሰላምና ፀጥታ የጋራ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።

''ሰላማዊ ፖለቲካ ለሀገራዊ ብልጽግና'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የምክክር መድረክ የሰላም ሚኒስቴርና የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ በጋራ አዘጋጅተውታል።

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ የተመዘገበው አስተማማኝ ሰላም ለልማት ስራዎች መፋጠን ምቹ መደላድል ፈጥሯል።


 

በመዲናዋ አስተማማኝ ሰላም ሊሰፍን የቻለው በህዝብ ተሳትፎ መሆኑን ጠቁመው ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ የሰላም ሠራዊት አባላትን በማሰልጠን ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም ልማቶች በፍጥነትና በጥራት እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።

በከተማዋ የተከበሩ በዓላት፣ የተካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጉባኤዎችና ውይይቶች በፍጹም ሰላም እንዲጠናቀቁ የጸጥታ ኃይሉና የህዝቡ ቅንጅት ውጤታማ እንደነበርም ገልጸዋል።

የሰላም እሴትን ለመገንባት በከተማዋ በሳምንት ሁለት ቀን የማህበረሰብ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ጨምረው ጠቅሰዋል።

ለወንጀል መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ቀድሞ በመለየት የመከላከል ስራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

የከተማዋን አስተማማኝ ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ ከአጎራባች የሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ኃላፊዋ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም