የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አገልግሎቶቹን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አገልግሎቶቹን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ አድርጓል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- የሀገሪቱን የገቢና ወጪ ንግድ ሥርዓት ለማቀላጠፍና ቁጥጥሩን ለማዘመን አገልግሎቶቹን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ማድረጉን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ በዲጂታል 2025 ስትራቴጂ በርካታ ውጤታማ የዲጂታላይዜሽን ተግባራትን አከናውናለች። ይህንንም አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችለው ዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው
በዲጂታል 2025 በርካታ ተቋማት አገልግሎታቸውን ያዘመኑ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዲጂታል የተደገፈ የተቀላጠፈ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
የጉምሩክ ኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ዲጂታል 2025 ተከትሎ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ላይ አተኩሮ በርካታ ውጤታማ ተግባራት በማከናወን የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረግ ተችሏል፡፡፡
በአሁኑ ወቅት ነጋዴዎች በማንኛውም ቦታ ሆነው የጉምሩክ ሥርዓትን መፈጸም የሚችሉበት የተቀናጀ የዲጂታል ሥርዓት መዘርጋት መቻሉን አስታውቀዋል።
ከ70 በላይ ተቋማትን በአንድ ላይ የሚያገናኘው የኤሌክትሮኒክ ሲንግል ዊንዶው ፕላትፎርም ተግባራዊ መድረጉን አንስተው፤ ይህም የንግድ ስራን ለማቀላጠፍ ትልቅ እመርታ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮሚሽኑን የክትትል አቅም ለማሳደግ ስማርት ቦርደር ማኔጅመንት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ሲሉም አንስተዋል፡፡
የኤሌክትሮኒክ ካርጎ ትራኪንግ ሲስተምን በመጠቀም ጭነቶች ካለባቸው መስመር እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝም ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል፡፡
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ ካሜራዎች በተለያዩ ስልታዊ ቦታዎች ላይ ተተክለው ውጤታማ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ምክትል ኮሚሽነሩ ኮሚሽኑ ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከባንኮችና ከሌሎች ፈቃጅና ተቆጣጣሪ ተቋማት ጋር በቴክኖሎጂ ትስስር መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡
በሀገር ውስጥ የታክስ ሥርዓትም የኢ-ፋይሊንግ እና የኢ-ፔይመንት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ ስራ ላይ ውለዋል ብለዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት በጂቡቲ የሚገኙ ሁለት ቅርንጫፎችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ያሉ 15 ቅርንጫፎች በሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የ24 ሰዓት አገልግሎት በቴክኖሎጂ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
ይህ መጠነ ሰፊ የዲጂታላይዜሽን ስራ የገቢና ወጪ ንግዱን ከማሳለጡ ባለፈ፣ የህግ ማስከበር ስራውን በቴክኖሎጂ የታገዘና ግልጽ አሰራረን ተግባራዊ በማድረግ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚደግፍ አስታውቀዋል።