ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂን በመገንባትና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ እያሳየችው ያለው እመርታ ዲጂታል ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን የዓለም አቀፍ ደህንነት ተመራማሪ እና የባሊሲሊ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጄራልድ ገለጹ።

ፕሮፌሰር አን ፊትዝ-ጄራልድ ለኢዜአ እንደገለፁት፣ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በዳታ ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችን ማምጣት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

ኢትዮጵያ በዲጂታል ትስስርና በመሠረተ ልማት አስደናቂ ሥራ እያከናወነች ነው

ይህም እንደ ግብርና፣ ደን ልማት እና ማዕድን ባሉ ዘርፎች ውስጥ ማካተቷ የወደፊት ኢኮኖሚዋን ለማጠናከር ቁልፍ መሳሪያ ነው ብለዋል።


 

ለዚህ ስኬት ሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI) እና የዳታ አያያዝ፣ የሳይበር ደህንነት ጥበቃ፣ የፈጠራ ባለቤትነትና የደረጃዎች ቁጥጥር እንዲሁም የኳንተም ቴክኖሎጂ የኮምፒውቲንግ አቅም ወሳኝነት እንዳላቸው አብራርተዋል።ይህም ለአፍሪካ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

በዘመናዊው ዓለም የኃይል ሚዛን የሚወሰነው በፈጠራ ባለቤትነት፣ በዳታ ቁጥጥር በተቀመጡ ደረጃዎች መሆኑንም አስረድተዋል።

ደረጃዎችን ማውጣት ለቴክኖሎጂ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ዘርፍ መሆን አለበት ያሉት ፕሮፌሰሯ፣ ኢትዮጵያ እነዚህን ደረጃዎች በፈጠራ ባለቤትነት በማስጠበቅ በዓለም መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንደምትችል ጠቁመዋል።

በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እያከናወነ ያለውን ስራ በማጠናከር የአፍሪካን  ድምፅ የሚያስተጋባ ይሆናል ብለዋል።


 

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ባለሙያ ባቻክ ኡጁሉ ኦማን በበኩላችው፣ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ የቴክኖሎጂ ፉክክር ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዓለምን ወቅታዊ እና ነባራዊ ሁኔታ ቀድማ በመገንዘብ የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጀመረችው ስራ እጅግ አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይም ብዙ የቤት ስራዎች ይጠበቅብናል ነው ያሉት።


 

በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ማበልፀጊያ እና የአዕምሮ ጥበቃ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ፈሊክስ ኢዴሳ፤ መንግስት በተለይም በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የኤአይ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ቴክኖሎጂን ከውጭ ተቋማት ጥገኝነት ነፃ እንደሚያወጣ ተናግረዋል።

ትልቅ የፈጠራ አቀም ላላቸው ኢትዮጵያውያን ወጣቶችም መልካም አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም