ቀጥታ፡

ብልጽግና በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል 

ደሴ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡-  ብልጽግና ፓርቲ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡ ተገለጸ።

በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ተግባራት የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት ያሳያሉ

ፓርቲው ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመወዳደሪያ ምልክቱንና ማኒፌስቶውን በደሴ፣  ወልዲያና ደብረ ብርሃን ከተሞች ለደጋፊዎችና ለአባላቱ ዛሬ አስተዋውቋል። 

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ መኮንን ፣ በፓርቲው የሚመራው መንግስት ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመገንባት በማዕድን፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ ዳኛው በበኩላቸው፣ ብልጽግና በመደመር ፍልስፍና የወል ትርክትና ህብረ ብሄራዊ አንድነት ላይ የተመሰረተች ሀገር ለመገንባት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የደሴ ከተማ  ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ አለማየሁ ፣ ፓርቲው ኢትዮጵያን ወደ ሁለንተናዊ ብልፅግና በማሸጋገር ላይ መሆኑን ለአባላትና ደጋፊዎች ገልጸዋል።

በተመሳሳይ  በብልጽግና ፓርቲ የወልዲያ ከተማ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ገብሬ በማስተዋወቂያ ፕሮግራሙ ላይ  ፓርቲው ለችግሮች ሳይበገር በርካታ ውጤቶችን ያስመዘገበ ነው ብለዋል።

በፓርቲው የሚመራው መንግስት በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተሞከሩ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ የሀገሪቱ ከፍታና የህዝቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በዚህም ባለፉት ዓመታት ሀገሪቱ ከፍ ብላ የምትታይባቸውን የህዳሴ ግድብን በማጠናቀቅ እንዲሁም በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በመገንባት ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል።

በበጋ ስንዴና ሌማት ትሩፋት ጨምሮ በሌሎችም የልማት መስኮች ለውጥ ማምጣቱን አመልክተዋል ።

ሰላምን ከማስፈን ጎን ለጎን የምግብ ሉአላዊነትን በማረጋገጥ ከተረጅነት የተላቀቀች ሀገር ለመፍጠር እየሰራ ያለው ስራ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ሰለሞን ጌታቸው እንደገለጹት፤ ፓርቲው  የተጀመሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለህዝብ ተጠቃሚነት እየሰራ ይገኛል።

ሌሎች የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችንም በማጠናቀቅ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የእድገት ምእራፍ ለማሸጋገር እየተጋ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም