ቀጥታ፡

በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ተግባራት የኢትዮጵያን ብልጽግና አይቀሬነት ያሳያሉ

ወላይታ ሶዶ ፤ የካቲት 19/2018 (ኢዜአ)፡- በብልጽግና ፓርቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያ ብልጽግናን አይቀሬነት እንደሚያሳዩ ተመላከተ።

የወላይታ ዞንና የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር በጋራ በመሆን  "ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር" በሚል መሪ ሃሳብ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የብልጽግና ፓርቲ ምልክት (የስንዴ ነዶ) እና ማኒፌስቶ ማስተዋወቂያ መርሃ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሄደዋል። 

ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገትና ስኬት ያስመዘገበ ፓርቲ ነው -ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)

በወቅቱም የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ እንደገለፁት፤ ብልጽግና ፓርቲ ሥር የሰደዱ  ስብራቶችን ለመጠገን የወሰዳቸው ስትራቴጂካዊ እርምጃዎች ስኬት የተመዘገበባቸው ናቸው።


 

ለአብነትም ማሕበረሰቡ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገር ተጨባጭ ሥራዎች የተሰሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን በተካሔደው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያም ለመጀመሪያ ጊዜ ስንዴን አምርቶ ወደ ውጭ መላክ መጀመሩንም ነው የጠቀሱት።

የስንዴ ነዶ የመደመር እሳቤያችን ተምሳሌት በመሆኑ አቅማችንን አሰባስበንና ጉልበታችንን አስተባብረን በአጭር ጊዜ ውስጥ ብልጽግናን ለማረጋገጥ እንሠራለን ሲሉም ተናግረዋል።

እስካሁን የተከናወኑ የልማት ስራዎች የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ ለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።


 

ፓርቲው የዜጎችን እና የሀገርን ክብር የሚያስጠብቅ የዲፕሎማሲ አካሄድን በመከተል ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ ያደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ እታገኝ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ብልጽግና የለውጥ ፍላጎቶችን መነሻ አድርጎ የተነሳ ሀገራችንን ከብተና ያዳነ ፓርቲ ነው ብለዋል።


 

በፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት ከተሞች እየዘመኑ እና እየተለወጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በፓርቲው መሪነት የተካሔዱ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የስንዴ ልማት፣ የሌማት ትሩፋት እና ሌሎችም ዘርፎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ካሉ በርካታ ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

የስንዴ ነዶ የመደመር፣ የአንድነትና የትብብር ምልክት ከመሆን ባሻገር ፓርቲያችን የነደፈውን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የመሸጋገር ውጥን በማሳካት ከልመና የመውጣታችንም ምልክት ነው ብለዋል።

በመሆኑም እንደ ነዶ እጅ ለእጅ ተያይዘን በመሥራት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከልመና የመውጣት ትልምን ለማሳካት መረባረብ አለብን ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም