ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገትና ስኬት ያስመዘገበ ፓርቲ ነው -ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገትና ስኬት ያስመዘገበ ፓርቲ ነው -ከንቲባ ተሾመ አዱኛ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ብልፅግና ፓርቲ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በሁሉም ዘርፍ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያስቀጥል አስደማሚ ስኬት ያስመዘገበ ፓርቲ መሆኑን የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) ገለጹ።
ብልፅግና ፓርቲ የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ማኒፌስቶውንና የስንዴ ነዶ የምርጫ ምልክቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ የካቲት 3 ቀን 2018 ዓ.ም ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
በሸገር ከተማ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም በከተማ ደረጃ የማኒፌስቶና የምርጫ ምልክት ይፋ ማድረጊያ መርኃ ግብር አካሂዷል።
የሸገር ከተማ ከንቲባ ተሾመ አዱኛ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ብልፅግና ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሁሉም ዘርፍ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያስቀጥል አስደማሚ ስኬት ያስመዘገበ ፓርቲ ነው።
ፓርቲው በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የትግበራ ሂደት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስክ ኢትዮጵያን አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ ስኬቶችን እያስገኘ መሆኑንም ገልጸዋል።
ሕብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የሰጠው ትኩረትም በዜጎች መካከል አሰባሳቢ ትርክትን በመገንባት አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ትልቅ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል።
በሸገር ከተማ በሁሉም የልማት መስኮች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ተወዳዳሪና ዘመናዊ ከተማን መገንባት የሚያስችሉ ስኬቶች በፓርቲው መሪነት መመዝገባቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም የከተማዋን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የሸገር ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አለማየሁ ቱሉ በበኩላቸው፤ የመደመር ፍልስፍና የወለደው የብልፅግና ፓርቲ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት አትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ስኬት አስመዝግቧል ብለዋል።
ፓርቲው በሸገር ከተማና በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለህዝብ ቃል የተገቡ የልማት ሥራዎችን በውጤታማነት መፈጸሙን ጠቅሰዋል።