ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጤና ተቋማትን ደረጃ ማሻሻል ቁልፍ ተግባር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጤና ተቋማትን ደረጃ ማሻሻል ቁልፍ ተግባር ነው
ኩታበር ፤ የካቲት 17/2018(ኢዜአ)፦ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጤና ተቋማትን ደረጃ ማሻሻል ቁልፍ ተግባር መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገለፁ።
በአውሮፓ ሕብረትና ዩኒሴፍ ድጋፍ ደረጃቸው የተሻሻሉ በደቡብ ወሎ ዞን የኩታበርና ሱሉላ ጤና ጣቢያዎች ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ የኢትዮጵያ የጤና ፖሊሲ በበሽታዎች ቅድመ መከላከልና አክሞ በማዳን ትኩረት አድርጓል።
ሚኒስቴሩ የጤና ተቋማትን ተደራሽነት በማስፋት፣ደረጃቸውን በማሻሻልና የህክምና ግብዓት በማሟላት ለዜጎች የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ በማደራጀትና ደረጃቸውን በማሻሻል አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በዚህም እናቶች በሰለጠነ ባለሙያ እንዲወልዱ በማድረግ በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም የሞት ምጣኔን መቀነስ ተችሏል ነው ያሉት።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል ማሕበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ሕብረተሰቡ የተሻለ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ ለጤና ተቋማት ደረጃ ማሻሻል ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አብዱልከሪም መንግሥቱ ናቸው።
በአውሮፓ ሕብረትና በዩኒሴፍ ድጋፍ በክልሉ በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች 35 ብሎክ ህንጻዎች ተገንብተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ገልጸዋል።
ይህም የጤና ተቋማትን ደረጃ ከማሻሻሉ ባለፈ የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል አንስተዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን፡ የዞኑን ሰላም ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ማሕበራዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ በተደረገ ጥረት የጤና አገልግሎት ላይ መሻሻል መምጣቱን አመልክተዋል።
የጤና ተቋማትን ደረጃ ለማሻሻልና ግብዓቶችን ለማሟላት የተሰራው ስራ የተገልጋዩን ፍላጎት ማሟላት ያስችላል ብለዋል።
የኩታበር ከተማ ነዋሪዋ ነኢማ መሀመድ፤ በአካባቢያቸው የሚገኘው ጤና ጣቢያ አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶለት ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ደስታቸውን ገልጸዋል።